1እናንት ዕፍረት የሌላችሁ ሕዝብ ሆይ፣ በአንድነት ተሰብሰቡ ተከማቹም፤
2የወሰነው ጊዜ ሳይደርስ፣ ቀኑ እንደ ገለባ ሳይጠራርጋችሁ፣ የያህዌ ቁጣ በእናንተ ላይ ሳይመጣና የያህዌ መዓት ቀን ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ፡፡
3እናንተ ትእዛዙን የምትፈጽሙ በምድር ያላችሁ ትሑታን ሁሉ ያህዌን ፈልጉ፤ ጽድቅንና ትሕትናንም ፈልጉ፤ በያህዌ ቀን ምናልባት ጥበቃ ታገኙ ይሆናል፡፡
4ጋዛ ባድማ ትሆናለች፤ አስቀሎናም ትፈራርሳለች፤ አሸዶድ በቀትር ባዶ ትሆናለች፤ አቃሮንም ትነቀላለች፡፡
5እናንተ በባሕር ዳርቻ የምትኖሩ የከሌታውያን ሰዎች ሆይ፣ የፍልስጥኤማውያን ምድር ከነዓን ሆይ፣ ያህዌ እናንተ ላይ ተናግሯልና ወዮላችሁ፤ ከእናንተ ማንም እስከማይተርፍ ድረስ አጠፋችኃለሁ፡፡
6የባሕሩ ዳርቻ የእረኞች መሰማርያና የበጐች በረት ይሆናል፡፡
7የባሕሩ ዳርቻ ከይሁዳ ቤት ለተረፉት ይሆናል፤ እነርሱም በዚያ መንጐቻቸውን ያሰማሩበታል፡፡ በአስቀሎና ቤቶች ውስጥ በምሽት ይተኛሉ፤ አምላካቸው ያህዌ ይጠብቃቸዋል፤ ሀብታቸውንም ይመልሳል፡፡
8በሕዝቤ ላይ የደረሰውን የሞዓብን ሕዝብ ፌዝና የአሞናውያንን ንቀት ሰምቻለሁ፤ ሕዝቤን ሰድበዋል፤ ርስታቸውን ለመውሰድም ዝተዋል፡፡
9ስለዚህ ይላል የሰራዊት ጌታ፣ የእስራኤል አምላክ ያህዌ፣ የሞዓብ ሕዝብ እንደ ሰዶም፣ አሞናውያንም እንደ ገሞራ ዐረም እንደ ዋጠው ቦታና እንደ ጨው ጉድጓድ ለዘላለም ጠፍ እንደሚሆኑ በሕያውነቴ እምላለሁ፤ ከሕዝቤ የተረፉት ይዘርፏቸዋል፤ ከወገኔ የተረፉትም ምድራቸውን ይወርሳሉ፡፡
10ከትዕቢታቸው የተነሣ፣ የሰራዊት ጌታ ያህዌ ሕዝብ ላይ በማፌዛቸውና እነርሱንም በመስደባቸው የሞዓብና የአሞን ሕዝብ ላይ ይህ ይሆናል፡፡
11እርሱ የምድሪቱን አማልክት በሚያጠፋበት ጊዜ፣ ያህዌ በእነርሱ ዘንድ የተፈራ ይሆናል፡፡ በባሕሩ ጠረፍና በየምድራቸው የሚኖሩ ሁሉ በያሉበት ያመልኩታል፡፡
12እናንተ ኢትዮጵያውያንም በሰይፌ ትገደላላችሁ፣
13የእግዚአብሔር እጅ ሰሜንን ይመታል፤ አሦርንም ያጠፋል፤ ነነዌን ባድማ ያደርጋል፤ እንደ ምድረ በዳም ትደርቃለች፡፡
14የአራዊት መንጋዎች፣ የአሕዛብ እንስሶች ሁሉ አሦር ውስጥ ያርፋሉ፤ ወፎችና ልዩ ልዩ ዐይነት ጉጉቶች በጉልላትዋ ላይ ይሰፍራሉ፡፡ ጩኸታቸው በየመስኮቱ ያስተጋባል፤ ከዝግባ የተሠሩ ተሸካሚዎች ተገልጠዋልና ቁራዎች በየደጃፎቻቸው ይጮኻሉ፡፡
15ይህች በልቧ «እኔ ብቻ ነኝ፤ ከእኔ በቀር ማንም የለም» ያለች ያለ አንዳች ፍርሃት ተደላድላ ትኖር የነበረች ከተማ ነች፡፡ ታዲያ፣ እንዴት የዱር አራዊት የሚኖሩባት ባድማ ሆና ቀረች? በአጠገቧ የሚያልፉ ሁሉ ያፌዙባታል፤ እጃቸውንም በንቀት ያወዛውዙባታል!