1እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።
2ምድርም ቅርፅ የሌላትና ባዶ ነበረች። ጥልቅ የሆነው ስፍራዋም በጨለማ ተውጦ ነበር። የእግዚአብሔርም መንፈስ በውሃው ላይ ሰፍፎ ነበር።
3እግዚአብሔርም፦ “ብርሃን ይሁን” አለ፤ ብርሃንም ሆነ።
4እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደሆነ አየ፤ ብርሃንኑም ከጨለማ ለየው።
5እግዚአብሔርም ብርሃኑን ‘ቀን’ ጨለማውን ደግሞ ‘ሌሊት’ ብሎ ጠራው። ቀኑ መሸ ሌሊቱም ነጋ አንድ ቀን ሆነ።
6እግዚአብሔርም፦ “በውሆች መካከል ጠፈር ይሁን፣ ውሆችንም ይለያዩ” አለ።
7እግዚአብሔር ጠፈርን አደረገና ከጠፈር በላይና ከጠፈር በታች ያሉትን ውሆች ለየ። እንደዚያም ሆነ።
8እግዚአብሔር ጠፈሩን ‘ሰማይ’ብሎ ጠራው። ቀኑ መሸ ሌሊቱም ነጋ ሁለተኛ ቀን።
9እግዚአብሔር፦ “ከሰማይ በታች ያለው ውሃ ወደ አንድ ስፍራ ይሰብሰብ፣ ምድሩም ይገለጥ” አለ። እንደዚያም ሆነ።
10እግዚአብሔርም ምድሩን ‘የብስ’፣ ወደአንድ ስፍራ የተሰበሰበውንም ውሃ ‘ባሕር’ ብሎ ጠራው። ይህም መልካም መሆኑን ተመለከተ።
11እግዚአብሔር፦ እንደ ዓይነታቸው ዘርን የሚያፈሩ ተክሎችን፣ በውስጣቸው ዘርን ያዘሉ የፍራፍሬ ዛፎችን እንደዓይነታቸው የሚያፈሩ አዝርዕትን ታብቅል” አለ። እንደዚያም ሆነ።
12ምድር እንደአይነታቸው የሚያፈሩ አዝርዕትን አበቀለች። ይህም መልካም እንደሆነ እግዚአብሔር ተመለከተ።
13ቀኑ መሸ፣ ሌሊቱም ነጋ ሶስተኛ ቀን ሆነ።
14እግዚአብሔር፦ “ቀኑን ከሌሊቱ ይለዩ ዘንድ በሰማይ ብርሃናት ይሁኑ። እነዚህ ብርሃናት የዓመት ወቅቶችን፣ ቀናትንና ዓመታትን የሚለዩ ምልክቶች ይሁኑ።
15ለምድርም ብርሃን ይሰጡ ዘንድ በሰማይ ላይ የሚገኙ ብርሃናት ይሁኑ” አለ። እንደዚያም ሆነ።
16እግዚአብሔር ታላቁ ብርሃን በቀን፣ ታናሹ ብርሃን በሌሊት ይሠለጥኑ ዘንድ ሁለት ታላላቅ ብርሃናትን አደረገ። ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ።
17ለምድርም ብርሃን ይሰጡ ዘንድና
18በቀንና በሌሊት ላይ እንዲሠለጥኑ እንደዚሁም ብርሃንን ከጨለማ እንዲለዩ በሰማይ አኖራቸው። እግዚአብሔር ይህ መልካም እንደሆነ ተመለከተ።
19ቀኑ መሸ፣ ሌሊቱም ነጋ አራተኛ ቀን ሆነ።
20እግዚአብሔር፦ “ውሆች በሕያዋን ፍጡራን የተሞሉ ይሁኑ፣ ወፎችም ከምድር በላይ ባለው በሰማይ ጠፈር ይብረሩ” አለ።
21እግዚአብሔር ታላላቅ የባሕር ፍጥረታትን እንደዚሁም በምድር የሚንቀሳቀሱ፣ በውሆች ውስጥ የሚርመሰመሱና በክንፎቻቸው የሚበሩ ወፎችን እንደዓይነታቸው ፈጠረ። እግዚአብሔር ይህ መልካም እንደሆነ ተመለከተ።
22እግዚአብሔርም፦ “ብዙ ተባዙ የባሕርን ውሆች ሙሉአቸው፣ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ” ብሎ ባረካቸው።
23ቀኑ መሸ፣ ሌሊቱም ነጋ አምስተኛ ቀን ሆነ።
24እግዚአብሔርም፦ “ምድር እንደወገናቸው ሕያው ፍጥረታትን ማለትም ከብቶችን፣ በምድር ላይ የሚሳቡትንና የምድር አራዊትን ታስገኝ” አለ። እንደዚያም ሆነ።
25እግዚአብሔር በየዓይነታቸው የምድር አራዊትን፣ በየዓይነታቸው ማናቸውንም በምድር የሚሳቡትን ፈጠረ።
26እግዚአብሔርም፦ “ሰውን በመልካችን እንደ አምሳላችን እንፍጠር፣ ሰዎችም በባሕር ዓሣዎች፣ በሰማይ በሚበሩ ወፎችና በምድር ላይ በሚሳቡ ማናቸውም ተሳቢ ፍጥረቶች ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ።
27እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ፣ በራሱም አምሳል ፈጠረው። ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።
28እግዚአብሔር ባረካቸው እንደዚህም አላቸው፦ “ብዙ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት ግዟትም። በባሕር ውስጥ ባሉት ዓሣዎች፣ በሰማይ ላይ በሚበሩት ወፎችና በምድር ላይ በሚንቀሳቀሱት ማናቸውም ሕያዋን ፍጥረቶች ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራችሁ”
29እግዚአብሔርም፦ “እነሆ፣ ምግብ ይሆኑላችሁ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ በውስጣቸው ዘርን ያዘሉ ማናቸውንም ተክሎችና በውስጣቸው ፍሬ ያላቸውን ማናቸውንም የፍራፍሬ ዛፎች ሰጥቻችኋለሁ።
30በምድር ላይ ለሚገኙ እንስሳት ሁሉ፣ በሰማይ ለሚበሩ ወፎች ሁሉ፣ እንዲሁም በምድር ላይ ለሚሳቡ ፍጥረታት ሁሉ ማለትም የሕይወት እስትንፋስ ላለበት ማንኛውም ፍጡር ማንኛውም ለምለም ተክል ምግብ እንዲሆናቸው ሰጥቻለሁ። እንደዚሁም ሆነ።
31እግዚአብሔር የፈጠረውን ማንኛውንም ነገር ተመለከተ። እነሆ፣ እጅግ መልካም ነበረ። ቀኑ መሸ፣ ሌሊቱም ነጋ ስድስተኛ ቀን ሆነ።