1ይህ በይሁዳ ንጉሥ በአሞን ልጅ በኢዮስያስ ዘመን፣ ወደ ሕዝቅያስ ልጅ፣ ወደ አማርያ ልጅ፣ ወደ ጐዶልያስ ልጅ፣ ወደ ኩሲ ልጅ፣ ወደ ሶፎንያስ የመጣ የያህዌ ቃል ነው፡፡
2«ማንኛውንም ነገር ከምድር ገጽ ፈጽሜ አጠፋለሁ! ይላል ያህዌ
3ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፤ የሰማይን ወፎችና የባሕር ዓሦች አጠፋለሁ፡፡ ሰውን ከምድር ገጽ በማስወግድበት ጊዜ ክፉዎች የፍርስራሽ ክምር ይሆናሉ ይላል ያህዌ፡፡
4እጄን በይሁዳና በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ሁሉ ላይ እዘረጋለሁ፡፡ የበአልን አምልኮ ርዝራዥ፣ የጣዖቶቹንና የአመንዝራ ካህናቱን ስም ከዚህ ቦታ አጠፋለሁ ስም ሁሉ ከዚህ ቦታ አጠፋለሁ፤
5በየቤቶቹ ጣራ የሰማይን ሰራዊት የሚያመልኩትን፣ በያህዌ ስም እየማሉ ደግሞም በሜልኮም የሚምሉትን ሕዝብ አጠፋለሁ፡፡
6ያህዌን ከመከተል ወደ ኃላ የሚሉትን፣ ያህዌን የማይፈልጉትንም ሆነ ከእርሱ ምሪት የማይፈልጉትን አጠፋለሁ፡፡»
7የያህዌ ቀን እየቀረበ ነውና በጌታ ያህዌ ፊት ጸጥ በሉ፤ ያህዌ መሥዋዕት አዘጋጅቷል፤ የጠራቸውንም እንግዶች ቀድሷል፡፡
8በያህዌ የመሥዋዕት ቀን መኳንንቱንና የንጉሡን ልጆች፣ እንግዳ ልብስ የሚለብሱትንም ሁሉ እቀጣለሁ፡፡
9በዚያን ቀን፣ በመድረኩ ላይ የሚዘልሉትን ሁሉ፣ የጌቶቻቸውን ቤት በዐመፅና በማጭበርበር የሚሞሉትንም ሁሉ እቀጣለሁ፡፡
10በዚያን ቀን ይላል ያህዌ፣ ከዓሣው በር ጩኸት፣ ከሁለተኛው አደባባይ ዋይታ፣ ከኮረብቶችም ታላቅ የጥፋት ድምፅ ይሰማል፡፡
11እናንት በገበያው ቦታ የምትኖሩ ዋይ በሉ፤ ነጋዴዎች ሁሉ ይደመሰሳሉ፤ በብር የሚነግዱትም ሁሉ ይጠፋሉ፡፡›
12በዚያ ዘመን፣ ኢየሩሳሌምን በመብራት እፈትሻለሁ፤ ወይን ጠጅ የሚያዘወትሩንና በልባቸው፣ «ክፉም ሆነ መልካም ያህዌ ምንም አያደርግም» የሚሉትን ሰዎች እቀጣለሁ፡፡»
13ሀብታቸው ይዘረፋል፤ ቤቶቻቸውም ይፈርሳሉ፤ ቤት ይሠራሉ፤ ሆኖም፣ አይኖሩበትም፤ ወይን ይተክላሉ የወይን ጠጁን ግን አይጠጡም፡፡
14ታላቁ የያህዌ ቀን ቀርቧል፤ እጅግ እየፈጠነ ነው፤ የያህዌ ቀን ድምፅ ጦረኞች አምርረው የሚያለቅሱበት ይሆናል፤
15ያ ቀን የቁጣ፣ የመከራና የጭንቀት፣ የጥፋትና የመፍረስ፣ የጨለማና የጭጋግ፣ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ይሆናል፡፡
16በዚያ ቀን በተመሸጉት ከተሞችና በረጃጅም ግንቦች ላይ የጦር መለከትና የማስጠንቀቂያ ድምፅ ይሰማል፡፡
17እንደ ዕውሮች እስኪደናበሩ ድረስ በሰዎች ላይ ታላቅ ጭንቀት አመጣለሁ፤ ያህዌ ላይ ኃጢአት አድርገዋልና ደማቸው እንደ ውሃ ይፈስሳል፤ ሬሳቸውም እንደ ጉድፍ የትም ይጣላል፡፡
18ብራቸውም ሆነ ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም፤ ያህዌ ቁጣውን በሚገልጥበት ቀን የቁጣው እሳት ምድርን ሁሉ ይበላል፤ ይህም የሆነው በምድር በሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ላይ በድንገት ጥፋት ስለሚመጣ ነው፡፡»