መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዘካርያስ 9

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ይህ በሴድራክና በደማስቆ ላይ የተነገረ የያህዌ ቃል ዐዋጅ ነው። የያህዌ ዐይኖች በሰው ልጆች ሁሉ እና በእስራኤል ነገዶች ሁሉ ላይ ናቸው።
2ይህ ዐዋጅ ደማስቆን የምታዋስናትን ሐማትንም ይመለከታል፤ በጣም ጥበበኞች ቢሆኑም ጢሮስንና ሲዶናንም ይመለከታል።
3ጢሮስ ለራሷ ምሽግ ሠርታለች፤ ብሩን እንደ ዐፈር፣ ንጹሑን ወርቅ እንደ መንገድ ላይ ትቢያ ቆልላለች።
4እነሆ፣ ጌታ ሀብቷን ይወስዳል፤ በባሕሩ ላይ ያላትንም ኀይል ይደመስሳል፤ እርሷም ፈጽማ በእሳት ትጸፋለች።
5አስቀሎና አይታ ትፈራለች! ጋዛም እጅግ ትሸበራለች! የአቃሮና ተስፋ ይጨነግፋል! ንጉሥ ከጋዛ ይጠፋል፤ አስቀሎና ከእንግዲህ መኖሪያ አትሆንም!
6ባዕዳን ቤታቸውን በአሽዶድ ያደርጋሉ፤ የፍልስጥኤማውያንን ትዕቢት አጠፋለሁ።
7ደሙን ከአፋቸው፣ የተከለከለውንም ምግብ ከጥርሶቻቸው መካከል አወጣለሁ። ያኔ እንደ ይሁዳ ነገድ የአምላካችን ትሩፋን ይሆናሉ፤ አቃሮንም እንደ ኢያቡሳዊ ይሆናል።
8እኔ ግን ቤቴን ከዘራፊዎች እጠብቃለሁ፤ ጨቋኝ እንግዲህ ምድሬን አይወርስም፤ አሁን ነቅቼ እጠብቃለሁና!
9አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፣ እጅግ ደስ ይበልሽ! አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፣ በደስታ ጩኺ! እነሆ ንጉሥሽ በጽድቅ ወደ አንቺ መጥቶ ያድንሻል። እርሱ ትሑት ነው፤ በእህያ ላይ ይቀመጣል፤ በአህያ ግልገል በውርንጫዋ ላይ ይቀመጣል።
10ከዚያም ከኤፍሬም ሰረገላን፣ ከኢየሩሳሌም ፈረስን አጠፋለሁ፤ ቀስት ከጦርነት ይሰበራል፤ ሰላምን ለሕዝቦች ይናገራል፤ ግዛቱ ከባሕር እስከ ባሕር ይሆናል፤ ከወንዝም እስከ ምድር ዳርቻ ይሆናል!
11ለአንቺ ደግሞ፣ ከአንቺ ጋር ካደረግሁት የደም ኪዳን የተነሣ እስረኞችሽን ውሃ ከሌለበት ጉድጓድ ነጻ እለቃቸዋለሁ።
12እናንተ የተስፋ እስረኞች ወደ ምሽጋችሁ ተመለሱ! አሁንም ቢሆን ዕጥፍ አድርጌ እንደምመልስላችሁ እናገራለሁ፤
13እንደ እኔ ቀስት ይሁዳን አጉብጫለሁ። ኤፍሬምን በፍላጻ ሞልቻለሁ። ጽዮን ሆይ፣ ልጆችሽን አስነሣለሁ፤ ግሪክ ሆይ በአንቺ ልጆች ላይ ይነሣሉ፤ እንደ ተዋጊ ሰይፍም አደርግሻለሁ!
14ያህዌ ለእነርሱ ይገለጣል፤ ፍላጻውም እንደ መብረቅ ይፈነጠራል! ጌታ ያህዌ መለከት ይነፋል፤ በቴማን ዐውሎ ነፋስ ይገሰግሣል።
15የሰራዊት ጌታ ያህዌ ይከልላቸዋል፤ ጠላቶቻቸውን ይደመስሳሉ፤ በድንጋይ ወንጭፍም ያሸንፋሉ። ይጠጣሉ፤ በወይን ጠጅ እንደ ሰከረ ሰው ይጮኻሉ፤ መሠዊያው ላይ እንዳሉ ዕቃዎች፣ እንደ መሠዊያው ማእዘኖች በወይን ይሚላሉ።
16በዚያ ቀን አምላካቸው ያህዌ ያድናቸዋል፤ ሕዝቡን የራሱ መንጋ ያደርጋቸዋል። አክሊል ላይ እንዳለ ዕንቁ፣ በገዛ ምድሩ ላይ ያብለጨልጫሉ።
17ምንኛ መልካም፣ ምንኛ ቆንጆ ይሆናሉ! እህል ወጣቶችን፣ ጣፋጭ ወይን ጠጅ ቆነጃጅቱን ያሳምራል!
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።