1የሰራዊት ጌታ የያህዌ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2የሰራዊት ጌታ ያህዌ እንዲህ ይላል፤ “ስለ ጽዮን እጅግ ቀንቻለሁ፤ ስለ እርሷ በታላቅ ቁጣ ነድጃለሁ!
3የሰራዊት ጌታ ያህዌ እንዲህ ይላል ወደ ጽዮን እመለሳለሁ፤ በኢየሩሳሌምም መካከል እኖራለሁ፤ ኢየሩሳሌም የእውነት ከተማ ትባላለች፤ የሰራዊት ጌታ የያህዌ ተራራም ቅዱሱ ተራራ ይባላል!
4የሰራዊት ጌታ ያህዌ እንዲህ ይላል ሽማግሌዎችና አሮጊቶች እንደ ገና በኢየሩሳሌም አደባባዮች ይሆናሉ፤ እያንዳንዱ ሰው በጣም ስለሚያረጅ በእጁ ምርኩዝ ይይዛል።
5የከተማዋ አደባባዮች በሚቦርቁ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ።
6የሰራዊት ጌታ ያህዌ እንዲህ ይላል፣ በዚያን ጊዜ ይህ ከተቀሩት ሕዝብ የማይቻል መስሎ ቢታይ እንኳ፣ በእኔ ዐይን ፊት የማይቻል ይመስላልን? ይህ የያህዌ ዐዋጅ ነው።
7የሰራዊት ጌታ ያህዌ እንዲህ ይላል። እነሆ እኔ ሕዝቤን ከፀሐይ መውጫና ከፀሐይ መጥለቂያ ምድር አድናለሁ!
8እንደ ገና አመጣቸዋለሁ፤ በኢየሩሳሌም መካከልም ይኖራሉ፤ እንደ ገና ሕዝቤ ይሆናሉ እኔም በእውነትና በጽድቅ አምላካቸው እሆናለሁ!
9የሰራዊት ጌታ ያህዌ እንዲህ ይላል፤ እናንተ ከነቢያት አፍ የወጡ ቃሎችን አሁን እየሰማችሁ ያላችሁ፣ የእኔ ቤት፣ የሰራውቲ ጌታ የእኔ የያህዌ ቤት መሠረት በተጣለ ጊዜ ቤተ መቅደሱ መሠራት እንዲችል እጆቻችሁን አበርቱ።
10ከእነዚያ ቀኖች በፊት ማንም እህል አልሰበሰበም ነበር፤ ለሰውም ሆነ ለእንስሳት የሚጠቅም ነገር አልነበረም፤ ከጠላት የተነሣ ለሚወጣም ሆነ ለሚገባ ሰው ሰላም አልነበረም ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው በባልንጀራው ላይ እንዲነሣ አድርጌ ስለ ነበር ነው።
11አሁን ግን እንደ ቀድሞው ዘመን አይሆንም፤ ከተረፈው ሕዝብ ጋር እሆናለሁ፤ ይህ የሰራዊት ጌታ የያህዌ ዐዋጅ ነው።
12የሰላም ዘር ይዘራል፤ ያንሰራራው ወይን ፍሬውን ይሰጣል፤ ምድሪቱም አዝመራዋን ታበረክታለች፤ ሰማያት ጠል ይሰጣሉ፤ የተፈረው ሕዝብ ይህን ሁሉ እንዲወርስ አድርጋለሁ።
13የይሁዳና የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ለሌሎች ሕዝቦች የመርገም ምሳሌ ሆናችሁ ነበር። ስለዚህ አድናችኋለሁ፤ በረከትም ትሆናላችሁ። አትፍሩ፤ እጃችሁም ይበርታ!
14የሰራዊት ጌታ ያህዌ እንዲህ ይላል፤ አባቶቻችሁ ቁጣዬን ባነሳሡ ጊዜ ያላንቻች ርኅራኄ ጥፋት ላመጣባቸው እንደ ወሰንሁ፣ ይላል የሰራዊት ጌታ ያህዌ
15አሁን ደግሞ ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ እንደ ገና መልካም ለማድረግ ወስኛለሁ፤ አትፍሩ!
16እናንተ ማድረግ ያለባችሁ እነዚህን ነው፤ እርስ በርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ፤ በአደባባዮቻችሁም እውነትን፣ ፍትሕንና ሰላምን አስፍኑ።
17በባልንጀራችሁ ላይ በልባችሁ ክፋትን አታውጠንጥኑ፤ የሐሰት መሓላን አትውደዱ፣ ምክንያቱም እኔ እነዚህን ሁሉ እጠላለሁ! ይህ የያህዌ ዐዋጅ ነው።”
18እንደ ገናም የሰራዊት ጌታ የያህዌ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
19አሰራዊት ጌታ ያህዌ እንዲህ ይላል፤ የአራተኛው ወር፣ የአምስተኛው ወር፣ የሰባተኛውና የአሥረኛው ወር ጾሞች ለይሁዳ ቤት የደስታ፣ የተድላና የሐሤት በዓሎች ይሆናሉ! ስለዚህ እውነትንና ሰላምን ውደዱ!
20የሰራዊት ጌታ ያህዌ እንዲህ ያላል፤ በተለያዩ ብዙ ከተሞች ያሉት እንኳ ሳይቀሩ እንደ ገና ሰዎች ይመጣሉ።
21የአንዱ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ሌላው ከተማ እየሄዱ፣ “ያህዌን ለመለመንና የሰራዊት ጌታ ያህዌን ለመፈለግ ኑ በፍጥነት እንሂድ፤ እኛ ራሳችንም ደግሞ እንሄዳለን” ይላሉ።
22ብዙ ሕዝብና ኀያላይ መንግሥታት የሰራዊት ጌታ ያህዌን ለመፈለግ ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣሉ፤ የያህዌንም ሞገስ ይለምናሉ!
23የሰራዊት ጌታ ያህዌ እንዲህ ይላል በእነዚያ ቀኖች ከየወገኑና ከየቋንቋው አሥር ሰዎች የእናንተን ልብስ ዘርፍ አጥብቀው በመያዝ፣ “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና፤ ከእናንተ ጋር እንሂድ! ይላሉ።