መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዘካርያስ 7

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ንጉሥ ዳርዮስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ካሴሉ በተባለው በዘጠነኛው ወር የያህዌ ቃል ወደ ዘካርያስ መጣ።
2የቤቴል ሰዎች እግዚአብሔርን ለመለመን ሳራሳርንና ሬጌሜሌክን አብረዋቸው ከነበሩ ሰዎች ላኩ።
3በሰራዊት ጌታ በያህዌ ቤት የነበሩትን ካህናትና ነቢያት፣ “ብዙ ዓመት እንዳደርግሁት በአምስተኛው ወር ማዘንና መጾም ይገባኛልን?” አሏቸው።
4ስለዚህ የሰራዊት ጌታ የያህዌ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
5“በምድሩ ላሉት ሕዝብ ሁሉ፣ ለካህናቱም እንዲህ በላቸው፤ በእነዚህ ሰባ ዓመታት አምስተኛና ሰባተኛ ወሮች የጾማችሁትና ያዘናችሁት በእውነት ለእኔ ነውን?
6የምትበሉትና የምትጠጡትስ ለራሳችሁ አይደለምን?
7በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች በሰላምና በብልጽግና ትኖር በነበረ ጊዜ የኔጌቭና የምዕራብ ተራሮች ግርጌ የሰው መኖሪያ በነበሩ ዘመን በቀደሙት ነቢያት የተነገረው የያህዌ ቃል ይኸው አልነበረምን?”
8የያህዌ ቃል እንደ ገና ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፣
9“የሰራዊት ጌታ ያህዌ እንዲህ ይላል፤ ‘በእውነተኛ ፍትሕና የኪዳን ታማኝነት፣ በምሕረትም ፍረዱ። እያንዳንዱ ሰው ለወንድሙ እንዲህ ያድረግ።
10መበለቶችንና ድኻ አደጎችን፣ መጻተኞችንና ድኻውን አታስጨንቋቸው፤ በልባችሁም አንዳችሁ በሌላው ክፉ አታስቡ!
11እነርሱ ግን መስማት አልፈለጉም፤ በእልኽኝነት ትከሻቸውን አሳበጡ። እንዳይሰሙ ጆሮአቸውን ደፈኑ።
12ሕጉንና የሰራዊት ጌታ የያህዌን ቃል ላለመስማት ልባቸውን እንደ ዐለት አጠነከሩ። በቀደሙት ዘመኖች በመንፈሱ፣ በነቢያትም አንደበት እነዚህን መልእክቶች ወደ ሕዝቡ ላከ። ሕዝቡ ግን መስማት አልፈለጉም፤ ስለዚህ ያህዌ በእነርሱ ላይ በጣም ተቆጣ።
13እርሱ ሲጠራቸው አልሰሙም። በተመሳሳይ መንገድ፣ ይላል የሰራዊት ጌታ ያህዌ “ወደ እኔ ይጣራሉ፤ እኔ ግን አልሰማም።”
14አይተዋቸው ወደማያውቁ ሕዝቦች ሁሉ በዐውሎ ነፋስ እበትናቸዋለሁ፤ ምድሪቱም በኋላቸው ባድማ ትሆናለች። ሕዝቡ መልካሚቱ ምድራቸውን ባድማ አድርገዋልና ማንም በምድሪቱ አያልፍም ወደዚያም አይመለስም።”
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።