1ከዚያም ዘወር ብዬ ዐይኖቼን አነሣሁ፤ እነሆም፣ የሚበር መጽሐፍ ተመለከትሁ!
2መልአኩም፣ “ምን ይታይሃል?” አለኝ። እኔም፣ “ርዝመቱ ሃያ ክንድ፣ ወርዱ አሥር ክንድ የሆነ መጽሐፍ ሲበር ይታየኛል” በማለት መለስሁ።
3እርሱም፣ “ይህ በምድር ሁሉ ላይ የሚመጣ መርገም ነው፤ የሚሰርቅ ሁሉ፣ በአንዱ በኩል በተጻፈው መሠረት ይጠፋል፤ በሐሰት የሚምል ሁሉ እንደ ተናገረው ቃል በሌላው ወገን በተጻፈው መሠረት ይጠፋል።
4እኔ መርገሙን አመጣዋለሁ፤ ይህ የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ዐዋጅ ነው። ወደ ሌባው ቤትና በስሜ በሐሰት ወደሚምለው ሰው ቤት ይገባል፤ በዚያም ይቀመጣል፤ ቤቱን፣ እንጨቱንና ድንጋዩን ያጠፋል።
5ከዚያም ከእኔ ጋር እየተነጋገረ የነበረው መልአክ መጥቶ፣ “ዐይንህን አንሥተህ እየመጣ ያለውን ተመልከት! አለኝ።
6እኔም፣ “ምንድን ነው?” አልኩት። እርሱም፣ “ይህ እየመጣ ያለውን ኢፋ የያዘ መስፈሪያ ነው፤ ይህ የምድሪቱ ሁሉ በደል ነው” አለኝ።
7ከዚያም ከእርሳስ የተሠራው ክዳን ተነሣ፤ የአፍ መስፈሪያው ውስጥ አንዲት ሴት ተቀምጣ ነበር!
8መልአኩም፣ “ይህች ዐመፃ ናት!” ብሎ መልሶ ወደ መስፈሪያው አስገባትና የእርሳሱን ክዳን አጋው።
9እነሆም፣ ዐይኔን አንሥቼ ሁለት ሴቶች ወደ እኔ ሲመጡ አየሁ፤ በክንፎቻቸውም ነፋስ ነበር፤ የሽመላ ክንፎችን የመሰሉ ክንፎች ነበሯቸው። መስፈሪያውን በምድርና በሰማይ መካከል አነሡት።
10በእኔም ጋር እየተነጋገረ የነበረውን መልአክ፣ “መስፈሪያውን ወዴት እየወሰዱት ነው?” አልሁት።
11እርሱም፣ “ቤተ መቅደስ ሊሠሩለት ወደ ባቢሎን ምድር ይወስዱታል፤ ቤተ መቅደሱ ዝግጁ ሲሆን፣ እዚያ በተዘጋጀለት ቦታ ይቀመጣል” አለኝ።