1በሴቶች መካከል እጅግ የተዋብሽዋ ሆይ፥ ውድሽ ወዴት ሄደ? ካንቺ ጋር እንድንፈልገው ውድሽ የሄደው በየትኛው አቅጣጫ ነው? ወጣቷ ለራሷ ስትናገር፥
2በአትክልቱ ሥፍራ መንጋውን ሊያሠማራ፥ አበቦችንም ሊሰበስብ፥ ውዴ ወደ አትክልቱ ሥፍራ፥ ወደ ቅመማ ቅመሞቹ መደቦች ወርዷል።
3እኔ የውዴ ነኝ፥ ውዴም የእኔ ነው፤ በአበቦቹ መካከል መንጋውን በደስታ ያሰማራል። የሴቲቱ አፍቃሪ እንዲህ ይላታል፥
4ውዴ ሆይ፥ እንደ ቴርሳ ቆንጆ ነሽ፥ እንደ ኢየሩሳሌም ውብ ነሽ፥ ሰንደቁን እንደያዘ ሠራዊት ታስፈሪያለሽ።
5አድክመውኛልና ዓይኖችሽን ከእኔ መልሺ። ፀጉርሽ ከገለዓድ ተራራ ቁልቁል የሚወርደውን የፍየል መንጋ ይመስላል።
6ጥርሶችሽ ከመታጠቢያ ሥፍራቸው የሚመጡትን የሴት በግ መንጋ ይመስላሉ። እያንዳንዱ መንታ ወልዷል፥ በመካከላቸውም መካን የለም።
7በመሸፈኛሽ ውስጥ ጉንጮችሽ ለሁለት የተከፈለ ሮማን ይመስላሉ። የሴቲቱ አፍቃሪ ለራሱ ሲናገር፥
8ስልሳ ንግሥቶች፥ ሰማንያ ቁባቶች፥ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ልጃገረዶች አሉ።
9እርግቤ፥ እንከን የሌለባት፥ ብቸኛዋ ናት፤ ለእናቷ ልዩ ልጅ፥ ለወለደቻት ሴትም የተመረጠች ነች። የሀገሬ ሴቶች ልጆች አይተው የተባረክሽ ነሽ አሏት፤ ንግሥቶችና ቁባቶችም ደግሞ አይተው አመሰገኗት፤ ንግሥቶቹና ቁባቶቹ እንዲህ አሏት፦
10የንጋት ብርሃን መስላ የምትወጣ፥ እንደ ጨረቃ ያማረች፥ እንደ ፀሐይ ያበራች፥ ሰንደቅ እንደ ያዘ ሠራዊት የምታስፈራ ይህቺ ማን ናት? የሴቲቱ አፍቃሪ ለራሱ ሲናገር፥
11በሸለቆው ውስጥ አዲስ የበቀለውን ለማየት፥ ወይኑ አፍርቶ እንደሆነ፥ ሮማኑም አብቦ እንደሆነ ለማየት፥ የለውዝ ተክል ወዳለበት ጥሻ ወረድሁ።
12በልዑሉ ሠረገላ እንደ ተቀመጥኩ ስለ ተሰማኝ፥ በጣም ደስ አለኝ። የሴቲቱ አፍቃሪ እንዲህ ይላል፥
13አንቺ ፍጹሟ ሴት፥ ተመለሽ፥ ተመለሽ፤ አተኩሬ እንዳይሽ ተመለሽ፥ እባክሽ ተመለሽ። ወጣቷ ሴት ፍቅረኛዋን እንዲህ ትለዋለች፥ በሁለት ረድፍ ጨፋሪዎች መካከል የምጨፍር ይመስል፥ ፍጹሟን ሴት ለምን ትክ ብለህ ታየኛለህ?