1አማትዋም ኑኃሚን ለእርስዋ “ልጄ ሆይ፣ ታርፊ ዘንድ፣ ነገሮችም ለአንቺ መልካም ይሆኑልሽ ዘንድ፣ የምታርፊበትን ስፍራ አልፈግልሽምን?” አለቻት፡፡
2አሁንም ቦዔዝ፣ ከወጣት ሴቶች ሰራተኞቹ ጋር የነበርሽበት ሰው፣ ዘመዳችን አይደለምን? ተመልከቺ፣ እርሱ ዛሬ ማታ በአውድማው ላይ ገብሱን በመንሽ ይበትናል፡፡
3ስለዚህ፣ ታጠቢ፣ ሽቶሽን ተቀቢ፣ ልብስሽን ቀይሪ፣ ወደ አውድማውም ውረጂ፡፡ ነገር ግን መብላትና መጠጣት እስኪጨርስ ድረስ ለሰውዮው አትታወቂ፡፡
4በተኛም ጊዜ፣ ወደ እርሱ መሄድ እንድትችይ እርሱ የተኛበትን ስፍራ ማስታወስሽን እርግጠኛ ሁኚ፣ እግሩን ግለጪ፣ በዚያም ተጋደሚ፡፡ ከዚያም የምታደርጊውን እርሱ ይነግርሻል፡፡
5ሩትም ለኑኃሚን “የተናገርሽኝን ሁሉ አደርጋለሁ” አለቻት፡፡
6ስለዚህ ወደ አውድማውም ወረደች፣ እርስዋም አማትዋ የሰጠቻትን ትዕዛዝ ተከተለች፡፡
7ቦዔዝም በበላና በጠጣ ጊዜ፣ ልቡም ደስ ባለው ጊዜ፣ በእህሉ ክምር ጫፍ ሊተኛ ሄደ፡፡ ከዚያም ሩት በቀስታ መጣች፣ እግሩንም ገለጠች፣ ተኛችም፡፡
8እኩለ ሌሊት በሆነ ጊዜ ሰውዮው ደነገጠ፡፡ እርሱም ዘወር አለ፣ አንዲትም ሴት እዚያው እግርጌው ተኝታ ነበረች፡፡
9እርሱም “ማን ነሽ? አለ፡፡ እርስዋም “እኔ ሴት አገልጋይህ ሩት ነኝ” አለችው፡፡ አንተ የቅርብ ዘመዴ ነህና ልብስህን በሴት አገልጋይህ ላይ ዘርጋ አለችው፡፡
10ቦዔዝም፣ “ልጄ ሆይ፣ በእግዚአብሔር የተባረክሽ ሁኚ፡፡ ከመጀመርያው ይልቅ በመጨረሻ ብዙ ደግነት አሳይተሻል፣ ምክንያቱም ድሃም ይሁን ባለጠጋ ከወጣት ወንዶች ከአንዳቸውም ጋር አልሄድሽምና” አላት፡፡
11አሁንም፣ ልጄ ሆይ፣ አትፍሪ! ያልሽውን ሁሉ አደርግልሻለሁ፣ ምክንያቱም በከተማየ ያሉ ሕዝብ ሁሉ ምግባረ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ ያውቃሉ፡፡
12አሁን እኔ የቅርብ ዘመድ መሆኔ እውነት ነው፤ ይሁን እንጂ ከእኔ የበለጠ የሚቀርብ ዘመድ አለ፡፡
13ዛሬ ሌሊት እዚህ ቆዪ፣ ነገም ጠዋት የዋርሳነትን ግዴታ እርሱ የሚፈጽም ከሆነ፣ መልካም ነው፣ የዋርሳነትን ግዴታ ይፈጽም፡፡ ነገር ግን እርሱ ለአንቺ የዋርሳነትን ግዴታ ባይፈጽም፣ ሕያው እግዚአብሔርን እኔ አደርገዋለሁ፡፡ እስከ ማለዳ ድረስ ተኚ፡፡
14ስለዚህ እስከ ማለዳ ድረስ በእግርጌው ተኛች፡፡ ነገር ግን አንዱ ሌላውን ማወቅ ከመቻሉ በፊት ተነሳች፡፡ ቦዔዝ “ሴት ወደ አውድማው መምጣትዋን ማንም እንዳያውቅ” ብሎ ነበርና፡፡
15ከዚያም ቦኤዝ “የለበስሽውን ልብስ አምጭና ያዢው” አላት፡፡ በያዘችም ጊዜ ስድስት ትልቅ መስፈሪያ ገብስ በልብሷ ላይ ሰፍሮ አሸከማት፡፡ የዚያን ጊዜ እርሱ ወደ ከተማ ሄደ፡፡
16ሩት ወደ አማትዋ በመጣች ጊዜ “ልጄ ሆይ፣ እንዴት ነሽ?” አለቻት፡፡ ሩትም ሰውዮው ለእርስዋ ያደረገውን ሁሉ ነገረቻት፡፡
17እርስዋም “እነዚህ ስድስት መስፈሪያ ገብስ እርሱ የሰጠኝ ናቸው፣ ‘ወደ አማትሽ ባዶ እጅሽን አትሂጂ’” ብሏልና፡፡
18ኑኃሚንም “ልጄ ሆይ፣ ይህ ጉዳይ እንዴት እንደሚሆን እስከምታውቂ ድረስ በዚህ ቆዪ፣ ሰውዮው ይህን ነገር ዛሬ እስኪጨርስ ድረስ አያርፍምና” አለች፡፡