መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሩት 2

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የኑኃሚን ባል አቤሜሌክ፣ በጣም ባለጠጋና ኃያል ሰው የሆነ ቦዔዝ የሚባል ዘመድ ነበረው፡፡
2ሞዓባዊቱ ሩት ኑኃሚንን “አሁን ልሂድና ወደ እርሻዎች ገብቼ እህል ልቃርም፡፡ በፊቱ ሞገስ የማገኘውን ሰው እከተላለሁ” አለቻት፡፡ ኑኃሚንም “ልጄ ሆይ፣ ሂጂ” አለቻት፡፡
3ሩት ሄደችና ከአጫጆችም በኋላ በእርሻ ውስጥ ቃረመች፡፡ እርስዋም የአቤሜሌክ ዘመድ ወደሆነው ወደ ቦዔዝ እርሻ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደረሰች።
4እነሆም፣ ቦዔዝ ከቤተ ልሔም መጣና ለአጫጆቹ “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን” አላቸው፡፡ እነርሱም “እግዚአብሔር ይባርክህ” ብለው መለሱለት፡፡
5ከዚያም ቦዔዝ በአጫጆቹ ላይ ተቆጣጣሪ የነበረውን አገልጋዩን “ይህች ወጣት ሴት የማን ናት?” አለው፡፡
6አጫጆቹንም የሚቆጣጠረው አገልጋይ “ይህች ወጣት ሞዓባዊት ከሞዓብ ምድር ከኑኃሚን ጋር የመጣች ናት” አለው፡፡
7እርስዋም ‘ከአጫጆቹ በኋላ እየተከተልሁ የእህል ቃርሚያ እንድቃርምና እንድለቅም እባክህ ፍቀድልኝ አለች’ አለው፡፡ ስለዚህ እርስዋም ወደዚህ መጣች፣ በቤት ጥቂት ከማረፍዋ በስተቀር፣ ከጠዋት ጀምራ እስከ አሁን ድረስ መቃረም ቀጥላለች፡፡”
8የዚያን ጊዜ ቦዔዝ ሩትን “ልጄ ሆይ፣ እኔን እያዳመጥሽኝ ነውን? ወደ ሌላ እርሻ ሄደሽ አትቃርሚ፤ ከእርሻየ አትሂጂ፣ ይልቁንም በዚህ ቆዪና ከወጠት ሴቶች ሰራተኞቼ ጋር አብረሽ ስሪ፡፡
9ዓይኖችሽ ሰዎቹ ወደሚያጭዱበት ስፍራ ብቻ ይመልከቱ፣ ሌሎቹንም ሴቶች ተከተያቸው፡፡ ሰዎቹን እንዳይነኩሽ አላዘዝኋቸውምን? ሲጠማሽ ወደ ውኃ ማሰሮዎቹ ሄደሽ ወንዶቹ ከቀዱት ውኃ መጠጣት ትችያለሽ” አላት፡፡
10ከዚያም በግንባርዋ መሬቱን በመንካት በቦዔዝ ፊት ሰገደች፡፡ እርስዋም “እኔ እንግዳ የሆንሁት ታስበኝ ዘንድ በአንተ ፊት ሞገስ ያገኘሁት ለምንድን ነው?” አለችው፡፡
11ቦዔዝም ለእርስዋ “ባልሽ ከሞተበት ጊዜ ጀምሮ የሰራሽው ስራ ሁሉ ለእኔ ተነግሮኛል፡፡ አማትሽን ለመከተልና ወደ ማታውቂው ሕዝብ ለመምጣት አባትሽንና እናትሽን የተወለድሽባትንም ምድር ትተሻል፡፡
12ስለ ስራሽ እግዚአብሔር ይክፈልሽ፡፡ ከክንፉ በታች መጠጊያ ካገኘሽበት ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ሙሉ ደመወዝሽን ተቀበይ” አላት፡፡
13እርስዋም “ጌታዬ ሆይ፣ ምንም እንኳ እኔ ከሴት አገልጋዮችህ እንደ አንዲቱ ባልሆንም አጽናንተኸኛልና፣ እኔን በደግነት አናግረኸኛልና በፊትህ ሞገስን ላግኝ” አለቸው፡፡
14በምሳም ጊዜ ቦዔዝ ለሩት እንዲህ አላት፡- “ወደዚህ ነይ፣ እንጀራም ብዪ፣ ጉርሻሽንም በሆምጣጤው ወይን አጥቅሺው፡፡” በአጫጆቹም አጠገብ ተቀመጠች፣ እርሱም የተጠበሰ እህል ሰጣት፣ እርስዋም እስክትጠግብ ድረስ በላች፣ የቀረውንም አተረፈች፡፡
15ለመቃረም ስትነሳ፣ ቦዔዝ ወጣት አገልጋዮቹን “በነዶው መካከልም እንድትቃርም ፍቀዱላት፣ ምንም መጥፎ ነገር ለእርስዋ አትናገሩአት፡፡
16ደግሞም ከነዶው ዘለላዎች አስቀርታችሁ በእርግጠኝነት ልተተዉላት ይገባል፣ እንድትቃርም ለእርስዋ ተዉላት፡፡ እርስዋንም አትውቀሱአት” ብሎ አዘዛቸው፡፡
17ስለዚህ በእርሻው ውስጥ እስከ ማታ ድረስ ቃረመች፡፡ ከዚያም የቃረመችውን እህል ወቃችው፣ የወቃችውም እህል አንድ የኢፍ መስፈሪያ ያህል ገብስ ሆነ፡፡
18እርስዋም ተሸክማው ወደ ከተማ ሄደች፡፡ አማትዋም የቃረመችውን አየች፡፡ ሩትም በልታ ከጠገበች በኋላ የተረፋትን የተጠበሰ እህል አውጥታ ለእርስዋ ሰጠቻት፡፡
19አማትዋም ለእርስዋ እንዲህ አለቻት፡-“ዛሬ የቃረምሽው ወዴት ነው? ለመስራትስ ወዴት ሄድሽ? የረዳሽ ሰው የተባረከ ይሁን፡፡” ከዚያም ሩት ለአማትዋ የቃረመችበት እርሻ ባለቤት ስለሆነው ሰው ነገረቻት፡፡ እርስዋም “ዛሬ ቃርሚያ የቃረምሁበት እርሻ ባለቤት ስሙ ቦዔዝ ይባላል” አለቻት፡፡
20ኑኃሚንም ለምራትዋ “ታማኝነቱን በሕያዋንና በሙታን ላይ ባልተወው በእግዚአብሔር የተባረከ ይሁን” አለቻት፡፡ ኑኃሚንም ደግሞ “ይህ ሰው ለእኛ የቅርብ ዘመዳችን ነው፣ ከሚቤዡን አንዱ ነው” አለቻት፡፡
21ሞዓባዊቱ ሩትም “በእርግጥም፣ እንዲህ አለኝ፣ ‘መከሬን ሁሉ እስኪጨርሱ ድረስ ከወጣት ወንዶች ሰራተኞቼ አትራቂ፡፡’”
22ኑኃሚንም ለምራትዋ ለሩት “ልጄ ሆይ፣ ከወጣት ሴቶች ሰራተኞቹ ጋር ብትወጪ መልካም ነው፣ በሌላ በየትኛውም እርሻ ጉዳት እንዳያገኝሽ” አለቻት፡፡
23ስለዚህም እርስዋ እስከ ገብሱና ስንዴው መከር መጨረሻ ድረስ ልትቃርም ወደ ቦዔዝ ሴቶች ሰራተኞች ተጠግታ ቆየች፡፡ እርስዋም ከአማትዋ ጋር ትኖር ነበር፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።