መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሩት 1

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1መሳፍንት ይገዙ በነበረበት ዘመን በምድሪቱ ላይ ራብ ነበረ። አንድ ከበተልሔም ይሁዳ የሆነ ሰው ከሚስቱና ከሁለቱ ልጆቹ ጋር ወደ ሞአብ አገር ሄደ፡፡
2የሰውዮው ስም አቤሜሌክ ይባል ነበር፣ የሚስቱም ስም ኑኃሚን ይባላል፡፡ የሁለቱም ወንዶች ልጆቹ ስም መሐሎንና ኬሌዎን፣ የይሁዳ ቤተልሔም ኤፍራታውያን ነበሩ፡፡ እነርሱም ወደ ሞዓብም አገር ደረሱና በዚያ ተቀመጡ፡፡
3የኑኃሚንም ባል አቤሜሌክ ሞተ እርስዋም ከሁለቱ ወንዶች ልጆችዋ ጋር ቀረች፡፡
4እነዚህ ወንዶች ልጆች ከሞዓባውያን ሴቶች ሚስቶችን ወሰዱ፤ የአንዷ ስም ዖርፋ ነበር፣ የሌላኛዋ ስም ደግሞ ሩት ነበረ። በዚያም ለአሥር ዓመታት ያህል ተቀመጡ፡፡
5ከዚያም መሐሎንና ኬሌዎን ሁለቱም ሞቱ፣ ኑኃሚንም ያለ ባልዋና ያለ ሁለቱ ልጆችዋ ብቻዋን ተለይታ ቀረች፡፡
6በዚያን ጊዜ ኑኃሚን ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ሞአብን ለመልቀቅና ወደ ይሁዳ ለመመለስ ወሰነች፡፡ እርስዋም በሞዓብ ምድር ሳለች እግዚአብሔር የተቸገሩትን ሕዝቡን እንደረዳቸውና መብልን እንደ ሰጣቸው ሰማች፡፡
7ስለዚህ እርስዋ ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ከነበረችበት ስፍራ ለቀቀች፣ ከዚያም ወደ ይሁዳ ምድር ለመመለስ መንገዱን ይዘው ወደታች ሄዱ፡፡
8ኑኃሚን ለምራቶችዋ “ሂዱ፣ እያንዳንዳችሁ ወደ እናታችሁ ቤት ተመለሱ፡፡ ለሞቱትና ለእኔ ታማኝነት እንዳሳያችሁን ሁሉ፣ እግዚአብሔር ለእናንተ ታማኝነቱን ያሳያችሁ፡፡
9ጌታ እያንዳንዳችሁን በሌላ ባል ቤት ዕረፍት ይስጣችሁ” አለቻቸው፡፡ ከዚያም ሳመቻቸው፣ እነርሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፡፡
10እነርሱም “አይሆንም! ከአንቺ ጋር ወደ ሕዝብሽ እንመለሳለን” አሉአት፡፡
11ኑኃሚን ግን “ልጆቼ ሆይ፣ ተመለሱ! ለምን ከእኔ ጋር ትሄዳላችሁ? ባሎቻችሁ ይሆኑ ዘንድ ለእናንተ የሚሆኑ ወንዶች ልጆች በማሕጸኔ አሁን አሉን?
12ልጆቼ ሆይ፣ ተመለሱ፣ በራሳችሁ መንገድ ሂዱ፤ ባል ለማግባት በጣም አርጅቻለሁና፡፡ ዛሬ ማታ ባል አገኛለሁ ብየ እንኳ ተስፋ ባደርግና ወንዶች ልጆችን ብወልድ፣
13እነርሱ እስኪያድጉ ድረስ ትጠብቃላችሁን? እየጠበቃችሁ አሁን ባል ሳታገቡ ትቀራላችሁን? አይሆንም፣ ልጆቼ ሆይ! ከእናንተ ይልቅ ሁኔታው እኔን እጅግ በጣም ያስመርረኛል፣ ምክንያቱም የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ወጥቶአልና፡፡
14በዚያን ጊዜ ምራቶችዋ ድምፃቸውንም ከፍ አደረጉና እንደገና አለቀሱ፡፡ ዖርፋም አማትዋን ሳመቻትና ተሰናበተቻት፣ ሩት ግን ተጠግታ ያዘቻት፡፡
15ኑኃሚንም “አድምጪኝ፣ እነሆ የባልሽ ወንድም ሚስት ወደ ሕዝብዋና ወደ አማልክትዋ ተመልሳለች፡፡ ከባልሽ ወንድም ሚስት ጋር አንቺም ተመለሽ” አለቻት፡፡
16ነገር ግን ሩት “ከአንቺ ርቄ እንድሄድ አታድርጊኝ፣ ወደምትሄጅበት እሄዳለሁና፤ በምትቆይበትም እቆያለሁና፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ ይሆናል፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፡፡
17በምትሞችበትም እሞታለሁ፣ በዚያም እቀበራለሁ፡፡ ከሞት በቀር እኛን አንድም ነገር ቢለየን እግዚአብሔር ይቅጣኝ፣ ከዚህም በላይ ያድርግብኝ” አለቻት፡፡
18ኑኃሚን ሩት ከእርስዋ ጋር ለመሄድ እንደ ወሰነች ባየች ጊዜ፣ ከእርስዋ ጋር መከራከር አቆመች፡፡
19ስለዚህ ሁለቱም ወደ ቤተ ልሔም ከተማ እስኪመጡ ድረስ ተጓዙ፡፡ ወደ ቤተ ልሔምም በደረሱ ጊዜ፣ ከተማው በሙሉ ስለ እነርሱ እጅግ በጣም ተደነቁ፡፡ ሴቶችም “ይህች ኑኃሚን ናትን?” አሉ፡፡
20እርስዋ ግን “ኑኃሚን ብላችሁ አትጥሩኝ፡፡ ሁሉን የሚችል አምላክ ሕይወቴን መራራ አድርጎታልና፣ ማራ በሉኝ” አለቻቸው፡፡
21በሙላት ሄድሁ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ወደ ቤቴ ባዶዬን እንደገና መለሰኝ፡፡ ታዲያ እግዚአብሔር አዋርዶኝ፣ ሁሉንም የሚችል አምላክ አስጨንቆኝ እያያችሁ ለምን ኑኃሚን ትሉኛላችሁ?” አለቻቸው፡፡
22ስለዚህ ኑኃሚንና ምራትዋ ሞአባዊት ሩት ከሞዓብ አገር ተመለሱ፡፡ እነርሱ የገብስ መከር በተጀመረ ጊዜ ወደ ቤተልሔም መጡ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።