1በክርስቶስ እውነትን እናገራለሁ እንጂ አልዋሽም፣ ህሊናዬ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሆኖ ይመሰክርልኛል፣
2ከፍተኛ ሀዘንና የማያቋርጥ ህመም በልቤ ውስጥ አለ።
3በሥጋ ዘሮቼ ስለሆኑት ወንድሞቼ ሲባል እኔ እራሴ በተረገምኩና ከክርስቶስ በተለየሁ ብዬ እመኛለሁ።
4እነርሱ እስራኤላውያን ናቸው። የልጅነት መብት ፥ክብሩ፥ቃል ኪዳኑ፥የህግ ስጦታው፥የአምልኮ ሥርዓቱ፥ የተስፋው ቃል አላቸው።
5ከሁሉ በላይና ለዘላለም የእግዚአብሔር ብሩክ የሆነው ክርስቶስ በሥጋ የመጣው ከአባቶቻቸው ነው። ለእርሱ ለዘላለም ምስጋና ይሁን። አሜን!
6ነገር ግን የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ተሻረ ማለት አይደለም። ምክንያቱም በእስራኤል የሚኖር ሁሉ እስራኤላዊ አይደለም።
7ወይም የአብርሀም ዘር ሁሉ የአብርሀም ልጆች አይደሉም። ነገር ግን «ዘርህ በይስሀቅ ይጠራልሀል» ተባለ።
8ይህም ማለት የሥጋ ልጆች የሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች አይደሉም። የተስፋው ቃል ልጆች ግን ዘሮቹ ሆነው ተቆጠሩ።
9የተስፋው ቃል «በዚህ ጊዜ ተመልሼ እመጣለሁ ለሳራም ልጅ ይሰጣታል» የሚል ነው።
10ይህ ብቻ አይደለም፣ ርብቃ ከአባታችን ከይስሀቅ
11ከጸነሰች በኋላ በምርጫ የሆነው የእግዚአብሔር ዓላማ ከሥራ የተነሳ ሳይሆን ከእርሱ ጥሪ የተነሳ ይጸና ዘንድ ልጆቹ ገና ሳይወለዱና ክፉም ሆነ ደግ ሳያደርጉ
12«ታላቁ ለታናሹ ይገዛል» ተብሎ ተነግሯት ነበር።
13ልክ «ያዕቆብን ወደድኩ ኤሳውን ጠላሁ» ተብሎ እንደተጻፈው ማለት ነው።
14እንግዲህ ምን እንላለን? በእግዚአብሔር ዘንድ የጽድቅ መጓደል አለ ማለት ነው? በጭራሽ አይደለም።
15ምክንያቱም ለሙሴ «የምምረውን እምራለሁ ለምራራለትም እራራለሁ» ብሎታል።
16ስለዚህም ምህረት ለፈለገ ወይም ለሮጠ ሳይሆን ምህረትን ከሚያሳይ ከእግዚአብሔር ነው።
17ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ስለፈርዖን ሲናገር «ኃይሌን በአንተ ላይ አሳይ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ይታወቅ ዘንድ ለዚህ ዋና ዓላማ አስነሳሁህ» ይላል።
18ስለዚህም ከፈለገ ለአንዱ ምህረትን ይሰጠዋል ሌላውን ደግሞ ግትር ያደርገዋል።
19«ታዲያ ሁልጊዜ ፈቃዱን የሚያደርግ ከሆነ ለምን ስህተትን ይፈልግብናል?» ትሉኝ ይሆናል።
20በአንጻሩ ለእግዚአሔር መልስ የምትስጥ አንተ ማን ነህ? የሸክላ ጭቃ ቅርጽ ያወጣለትን ሰው ለምን እንደዚህ አድርገህ ሰራኽኝ ሊለው ይችላልን? ።
21ሸክላ ሰሪው ከዚያው ጭቃ አንዱን ለየት ባለ ቀን አገልግሎት ላይ የሚውል ዕቃ ሌላውን ደግሞ በየቀኑ አገልግሎት የሚሰጥ ዕቃ አድርጎ ሊሰራው በሸክላ ጭቃው ላይ ሥልጣን የለውም እንዴ?
22ቁጣውን ሊያሳይና ኃይሉ እንዲታወቅ የሚፈልገው እግዚአብሔር ለጥፋት የተዘጋጁትን የቁጣ ዕቃዎችአብዝቶ ሊታገሳቸው ቢፈልገስ?
23ይህን ያደረገው አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው የምህረት ዕቃዎቹ ላይ ክብሩን ሊያሳይ ቢሆንስ?
24ይህንን ለአይሁድ ብቻ ሳይሆን ከአህዛብ ለተጠራን ለእኛም ቢያደርገውስ?
25በትንቢት ሆሴዕም ላይ «ህዝቤ ያልሆነውን ህዝቤ ብዬ ያልተወደደችውንም የተወደደች ብዬ እጠራለሁ።
26'ህዝቤ አይደላችሁም በተባሉበት በዚያው ቦታ 'የህያው እግዚአብሔር ልጆች' ይባላሉ» እንደሚለው ነው።
27ኢሳያስ ስለእስራኤል «የእስራኤል ልጆች ብዛት እንደ ባህር አሸዋ ቢሆን እንኳ የሚድኑት ግን ትሩፋን ናቸው» ብሎ ይጮኸል።
28ምክንያቱም እግዚአብሔር ቃሉን በምድር ላይ ሙሉ በሙሉ ፈጥኖ ይፈጽማል።
29ይህም ኢሳያስ ቀደም ሲል «የሠራዊት ጌታ ዘር ባያስቀርልን ኖሮ እንድ ሰዶም በሆንን እንደ ገሞራም በሆነብን ነበር» እንዳለው ነው።
30እንግዲህ ምን እንላለን? ለጽድቅ ያልሮጡት አህዛብ በእምነት የሆነውን ጽድቅ አገኙ።
31ለጽድቅ ህግ የተጉት እስራኤል ግን ወደዚያ ሊደርሱ አልቻሉም።
32ለምን አልደረሱም? ምክንያቱም ጽድቅን የፈለጉት በእምነት ሳይሆን በሥራ ስለሆነ ነው። በማሰናከያው ድንጋይ ተሰናከሉበት።
33«በጽዮን የማሰናከያ ድንጋይና የዕንቅፋት ዐለት አስቀምጣለሁ በእርሱ የሚያምን አያፍርም» ተብሎ እንደተጻፈው ነው።