መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሮሜ 8

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም።
2ምክንያቱም በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ያለው የመንፈስ ቅዱስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነጻ አውጥቶኛል።
3በሥጋ ድካም ምክንያት ሕግ ሊፈጽመው ያልተቻለውን እግዚአብሔር ፈጽሞታል። እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአታዊ ሥጋ ምሳሌ ለኃጢአት መሥዋዕት ይሆን ዘንድ ልኮ ኃጢአትን በሥጋው ኮነነ።
4ይህንንም ያደረገው እንደ መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ በማንመላለስ በእኛ የሕጉ ትዕዛዛት ይፈጸሙ ዘንድ ነው።
5እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ ስለሥጋዊ ነገሮች ያስባሉ፥እንደ መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን ስለመንፈስ ቅዱስ ነገሮች ያስባሉ።
6የሥጋ አስተሳሰብ ሞት ሲሆን የመንፈስ ቅዱስ አስተሳሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።
7ይህ የሆነበት ምክንያት የሥጋ አስተሳሰብ ለእግዚአብሔር ሕግ ስለማይገዛ፥መገዛትም ስለማይችል የእግዚአብሔር ጠላት በመሆኑ ነው።
8በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ለማስደሰት አይችሉም።
9ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ውስጥ መኖሩ እውነት ከሆነ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። ነገር ግን የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ማንም ቢሆን ይህ የእርሱ ወገን አይደለም።
10ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢኖር ሥጋ በኃጢአት ምክንያት ምውት ነው፥ መንፈስ ግን በጽድቅ ምክንያት ህያው ነው።
11ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ውስጥ ቢኖር ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በውስጣችሁ በሚኖረው በቅዱስ መንፈሱ አማካይነት ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል።
12ስለዚህ ወንድሞች ሆይ ዕዳ አለብን፥ነገር ግን እንደ ሥጋ ፈቃድ ልንኖር ለሥጋ አይደለም።
13እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ መሞታችሁ አይቀርም፥የሥጋን ሥራ በመንፈስ ቅዱስ ብትገድሉ ግን በሕይወት ትኖራላችሁ።
14በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው።
15ተመልሳችሁ እንድትፈሩ የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁም። ይልቅ የተቀበላችሁት "አባ፥አባት" ብለን የምንጮህበትን የልጅነትን መንፈስ ነው።
16የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን መንፈስ ቅዱስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል።
17ልጆች ከሆንን ወራሾችም ነን፥ማለትም የእግዚአብሔር ወራሾች ነን። ከእርሱ ጋር እንድንከብር በርግጥ አብረነው ደግሞ መከራን ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን የምንወርስ ነን።
18የአሁኑ ዘመን መከራ ሊገለጥልን ካለው ክብር ጋር ሊነጻጸር እንደማይገባው አስባለሁ።
19ምክንያቱም ፍጥረት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በናፍቆት ስለሚጠባበቅ ነው።
20ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቷልና ይህም ባስገዛው ፈቃድ እንጂ በራሱ ፈቃድ አይደለም። አስተማማኙ ተስፋም
21ፍጥረት ራሱ ከመበስበስ ባርነት ነጻ ወጥቶ ወደ እግዚአብሔር ልጆች የክብር ነጻነት ይደርስ ዘንድ ነው።
22አሁን እንኳን መላው ፍጥረት አብሮ በመቃተትና በምጥ ጣር ላይ መሆኑን እናውቃለን።
23ይህም ብቻ አይደለም፥ነገር ግን የመንፈስ ቅዱስ የመጀመሪያው ፍሬ ያለን እኛ፥የሰውነታችን ቤዛ የሚሆነውን ልጅነታችንን እየተጠባበቅን እኛ ራሳችን እንኳን በውስጣችን እንቃትታለን።
24የዳንነው በዚህ ተስፋ ነው። ነገር ግን ተስፋ የምናደርገው የማይታየውን ነው፥የሚያየውንማ ማን በተስፋ ይጠባበቃል?
25ገና ያላየነውን ተስፋ የምናደርግ ከሆነ ግን እንግዲያው በትዕግስት እንጠባበቀዋለን።
26እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በድካማችን ውስጥ ያግዘናል። እንዴት መጸለይ እንደሚገባን ስለማናውቅ መንፈስ ቅዱስ ራሱ በቃላት ሊገለጥ በማይቻል መቃተት ስለ እኛ ይማልድልናል።
27መንፈስ ቅዱስ ስለ አማኞች እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለሚማልድ ልብን የሚመረምረው እግዚአብሔር የመንፈስ ቅዱስን ሃሳብ ያውቃል።
28እግዚአብሔርን ለሚወዱት፥ በዓላማው ለተጠሩት ለእነርሱ ሁሉን ነገር አጣጥሞ ለመልካም እንደሚሠራላቸው እናውቃለን።
29ምክንያቱም አስቀድሞ ያወቃቸውን እነርሱን በብዙ ወንድሞች መካከል በኩር ይሆን ዘንድ የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወሰነ።
30አስቀድሞ የወሰናቸውን ደግሞ ጠራቸው። የጠራቸውን ደግሞ አጸደቃቸው። ያጸደቃቸውን ደግሞ አከበራቸው።
31እንግዲህ ስለእነዚህ ነገሮች ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?
32ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለሁላችን አሳልፎ የሰጠው እርሱ እንዴት ሁሉን ነገር ደግሞ ከልጁ ጋር በነጻ አይሰጠንም?
33እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይኮንናቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው።
34የሚኮንንስ ማነው? ስለ እኛ የሞተው፥ ይልቁንም ደግሞ ከሞት የተነሣው ክርስቶስ ነው። እርሱ ከእግዚአብሔር ጋር በክብር ሥፍራ ይገዛል፥ስለ እኛም እየማለደልን ያለው እርሱ ነው።
35ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት ወይስ ራብ ወይስ ራቁትነት ወይስ አደጋ ወይስ ሰይፍ ይለየናልን?
36"ቀኑን ሙሉ ስለአንተ ብለን እንገደላለን። እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን" ተብሎ እንደተጻፈው ነው።
37በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ውስጥ በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።
38ሞት ቢሆን ሕይወት፥ መላእክት ቢሆኑ መንግሥታት፥አሁን ያሉት ነገሮች ወይም ሊመጡ ያሉት ቢሆኑ፥ ኃይላት ቢሆኑ፥
39ከፍታም ቢሆን ዝቅታ፥ የትኛውም ሌላ ፍጥረት ቢሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየኝ እንደማይችል ተረድቻለሁ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።