መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሮሜ 7

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ወንድሞች ሆይ፥ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ ሕግ እንደሚገዛው አታውቁምን? ይህንን የምለው ስለ ሕግ ለሚያውቁት ነው።
2ያገባች ሴት ባሏ በሕይወት እስካለ ድረስ ለእርሱ በሕግ የታሰረች ነች፥ባሏ ቢሞት ግን ከጋብቻ ሕግ ነጻ ትሆናለች።
3እንግዲህ ባሏ በሕይወት እያለ ከሌላ ወንድ ጋር ብትኖር አመንዝራ ትባላለች። ባሏ ቢሞት ግን ከሕጉ ነጻ ስለሆነች ከሌላ ወንድ ጋር ብትኖርም አመንዝራ አትሆንም።
4ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ፥እናንተም በክርስቶስ ሥጋ ለሕግ ምውት ተደርጋችኋል። ይኸውም ለእግዚአብሔር ፍሬ እናፈራ ዘንድ ከሌላው ማለትም ከሙታን ከተነሣው ጋር እንድትተባበሩ ነው።
5በሥጋ በነበርንበት ጊዜ ኃጢአታዊ ምኞት በሕግ በኩል ሞትን ሊያፈራ በሰውነታችን ክፍሎች ይሠራ ነበር።
6አሁን ግን ከሕግ ነጻ ተደርገናል። ተይዘን ለነበርንበት ለዚያ ሞተናል።ይኸውም በአሮጌው ፊደል ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ እንድናገለግል ነው።
7እንግዲህ ምን እንላለን? ሕጉ ራሱ ኃጢአት ነውን? አይደለም። ይሁንና በሕግ በኩል ባይሆን ኖሮ ኃጢአትን አላውቅም ነበር። ሕጉ "አትጎምጅ" ባይል ኖሮ መጎምጀትን አላውቅም ነበር።
8ነገር ግን ኃጢአት በትዕዛዛት አማካይነት ዕድል አገኘና መጎምጀትን ሁሉ በውስጤ አመጣ። ምክንያቱም ኃጢአት ያለ ሕግ ምውት ስለሆነ ነው።
9በአንድ ወቅት ያለ ሕግ ሕያው ነበርኩ፥ትዕዛዝ በመጣ ጊዜ ግን እኔ ሞትኩኝና ኃጢአት ህያው ሆነ።
10ሕይወትን እንዲያመጣ የተሰጠው ትዕዛዝ ለእኔ ሞት ሆነ።
11ምክንያቱም ኃጢአት በሕግ አማካይነት ዕድል አግኝቶ አታሎኛል። በትዕዛዝ አማካይነትም ገደለኝ።
12በመሆኑም ሕጉ ቅዱስ ነው፥ትዕዛዙም ቅዱስ፥ጻድቅና በጎ ነው።
13ስለዚህ በጎ የሆነው እርሱ ለእኔ ሞት ሆነብኝን? አይደለም። ነገር ግን ኃጢአት በጎ በሆነው በእርሱ አማካይነት ኃጢአትነቱ ይታወቅ ዘንድ በእኔ ሞትን አመጣብኝ። ይህ የሆነው በሕግ አማካይነት ኃጢአት ያለ ልክ ኃጢአታዊ ይሆን ዘንድ ነው።
14ሕጉ መንፈሳዊ መሆኑን እናውቃለንና እኔ ግን ሥጋዊ ነኝ። ለኃጢአት ባርነት ተሽጫለሁ።
15በርግጥ የማደርገውን አላውቅም። ለማድረግ የምፈልገውን አላደርግም፥ለማድረግ የምጠላውን ግን ያንኑ አደርጋለሁ።
16ለማድረግ የማልፈልገውን የማደርግ ከሆንሁ ሕጉ መልካም ስለመሆኑ እስማማበታለሁ።
17አሁን ግን ያንን የሚያደርገው በእኔ የሚኖረው ኃጢአት ነው እንጂ እኔ አይደለሁም።
18በእኔ ማለትም በሥጋዬ ውስጥ ምንም መልካም ነገር እንደሌለ አውቃለሁ። መልካም የማድረግ ፍላጎቱ አለኝ፥ነገር ግን ላደርገው አልችልም።
19የምፈልገውን ያንን መልካሙን አላደርግም ክፉውን፥ያንን የማልፈልገውን ግን አደርጋለሁ።
20ለማድረግ የማልፈልገውን የማደርግ ከሆነ እንግዲህ አሁን ያንን የሚያደርገው በእኔ ውስጥ የሚኖረው ኃጢአት እንጂ እኔ አይደለሁም።
21እንግዲህ መልካም የሆነውን ለማድረግ የሚፈልግ ሕግ በውስጤ እንዳለ አያለሁ፥ነገር ግን በተግባር በውስጤ ያለው ክፋት ሆኖ አገኘዋለሁ።
22በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛል።
23ነገር ግን በሰውነቴ ክፍሎች ውስጥ ሌላ ሕግ አያለሁ። እርሱም በአዕምሮዬ ውስጥ ያለውን አዲሱን ሕግ በመቃወም ይዋጋል። በሰውነት ክፍሎቼ ውስጥ ባለ የኃጢአት ሕግ ይማርከኛል።
24እኔ ምስኪን ሰው ነኝ! ለሞት ከሚዳርገኝ ከዚህ ሰውነት ማን ይታደገኛል?
25እንግዲያውስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! እኔ ራሴ በአእምሮዬ የእግዚአብሔርን ሕግ አገለግላለሁ። ሆኖም በሥጋ የማገለግለው የኃጢአትን ሕግ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።