1በእምነት ስለ ጸደቅን በጌታችን በኢየሱስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም አለን።
2እኛም ደግሞ በእርሱ በኩል አሁን ወደቆምንበት ወደዚህ ጸጋ በእምነት መቅረብ አለን። በእግዚአብሔር ክብር ውስጥ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ እግዚአብሔር ስለወደፊቱ በሰጠን ተስፋ በመተማመን ደስ ይለናል።
3ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን በመከራዎቻችን ደግሞ ደስ ይለናል። መከራ መጽናትን እንደሚያደርግ እናውቃለን።
4መጽናት ተቀባይነትን፥ ተቀባይነትም ስለ ወደፊቱ መተማመኛን ያስገኛል።
5በተሰጠን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የእግዚአብሔር ፍቅር ወደ ልባችን ውስጥ ስለፈሰሰ ይህ ተስፋ ሐዘን የለበትም።
6ክርስቶስ በትክክለኛው ጊዜ ለኃጢአተኞች የሞተው እኛ ገና ደካሞች እያለን ነበር።
7ስለ ጻድቅ ሰው የሚሞት ከስንት አንዱ ነው። ይህም ማለት ስለ ደግ ሰው ለመሞት የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል።
8ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች እያለን ክርስቶስ ስለ እኛ መሞቱ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያረጋግጣል።
9እንግዲህ አሁን በደሙ ስለ ጸደቅን ይበልጡኑ በእርሱ ከእግዚአብሔር ቁጣ እንድናለን።
10ጠላቶች እያለን በልጁ ሞት ከእግዚአብሔር ጋር ከታረቅን ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን።
11ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን አሁን ይህንን ዕርቅ ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እኛ ደግሞ በእግዚአብሔር ደስ ይለናል።
12ስለዚህ በአንድ ሰው አማካይነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፥እንደዚሁም ሞት በኃጢአት አማካይነት ገባ። ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ወደ ሰው ሁሉ ደረሰ።
13ሕግ እስኪመጣ ድረስ ኃጢአት በዓለም ነበረ፥ነገር ግን ሕግ በሌለበት ኃጢአት አይቆጠርም።
14ይሁንና ሊመጣ ላለው ምሳሌ የሆነው የአዳምን አይነት ያለመታዘዝ ኃጢአት ባላደረጉት ላይ እንኳን ሳይቀር ከአዳም እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ።
15ነጻ ስጦታው ግን እንደ መተላለፉ አይደለም። በአንዱ መተላለፍ ብዙዎች ከሞቱ የእግዚአብሔር ጸጋና በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ በኩል የሆነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዛ።
16ስጦታው እንደተሰራው ኃጢአት ውጤት አይደለም። በአንድ ወገን በአንዱ ሰው መተላለፍ ምክንያት የኩነኔ ፍርድ መጣ። በሌላ ወገን ግን ጽድቅን የሚያስገኘው ነጻ ስጦታው ከብዙ መተላለፍ በኋላ መጣ።
17በአንዱ ሰው መተላለፍ ሞት በእርሱ በኩል ከነገሠ የጸጋን ብዛትና በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት በኩል የጽድቅን ስጦታ የተቀበሉት አብልጠው ይነግሳሉ።
18እንግዲህ በአንዱ መተላለፍ በኩል ሰዎች ሁሉ ወደ ኩነኔ እንደመጡ እንዲሁ በአንዱ የጽድቅ ሥራ ለሰዎች ሁሉ የሕይወት መጽደቅ መጣ።
19በአንድ ሰው አለመታዘዝ በኩል ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ እንዲሁ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።
20ነገር ግን ሕግ ከጎን በመግባቱ መተላለፍ በዛ። ይሁን እንጂ ኃጢአት በበዛበት በዚያ ጸጋ ይበልጡኑ በዛ።
21ኃጢአት በሞት እንደ ነገሠ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዘላለም ሕይወት ጸጋው በጽድቅ አብልጦ እንዲነግሥ ይህ ሆነ።