1እንግዲህ በስጋ አባታችን የሆነው አብርሃም ምን አገኘ እንበል?
2አብርሃም በሥራ ጸድቆ ቢሆን ኖሮ ለመመካት ምክንያት በኖረው ነበር፥ትምክህቱ ግን በእግዚአብሔር ፊት አይደለም።
3ቅዱሱ መጽሐፍ ምን ይላል? "አብርሃም እግዚአብሔርን አመነ፥ይህም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት" ይላል።
4ለሚሠራ ሰው ደሞዙ እንደ ተገቢ መብቱ እንጂ እንደ ነጻ ስጦታ አይቆጠርለትም።
5ነገር ግን ለማይሠራ ይልቁንም ኃጢአተኛውን በሚያጸድቅ ለሚያምን ለእርሱ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል።
6ዳዊት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ሥራ ጽድቅን በሚቆጥርለት ሰው ላይ በረከትን ይናገራል።
7እርሱም፤ "መተላለፋቸው የተተወላቸው፥ ኃጢአታቸውም የተከደነላቸው እነርሱ የተባረኩ ናቸው።
8ጌታ ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ያ ሰው የተባረከ ነው።" ብሏል።
9እንግዲህ ይህ በረከት የተነገረው በተገረዙት ላይ ብቻ ነው ወይስ ደግሞ ባልተገረዙትም ላይ? "ለአብርሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት" እንላለን።
10ታዲያ እንዴት ነበር የተቆጠረለት? አብርሃም ከመገረዙ በፊት ወይስ በኋላ? ከመገረዙ በፊት እንጂ ከተገረዘ በኋላ አልነበረም።
11አብርሃም የመገረዝን ምልክት ተቀበለ። ይህም ከመገረዙ በፊት አስቀድሞ በእምነት ላገኘው ጽድቅ ማኅተም ነበር። የዚህ ምልክት ውጤት ምንም እንኳን ባይገረዙ ለሚያምኑ ሁሉ አባት መሆኑ ነው። ይኸውም ጽድቅ ይቆጠርላቸዋል ማለት ነው።
12በተጨማሪም ይህ ማለት አብርሃም አባት የሆነው በመገረዝ በኩል ለሚመጡት ብቻ ሳይሆን ነገር ግን የአባታችን የአብርሃምን ምሳሌነት ለሚከተሉትም ነው። ይህም ሳይገረዝ በፊት በነበረው እምነት ነው።
13ዓለምን የሚወርሱበት ለአብርሃምና ለዘሩ የተሰጠው ይህ ተስፋ በሕግ በኩል የተሰጠ አልነበረም። ይልቅ ይህ በእምነት በኩል የተገኘ ጽድቅ ነበር።
14በሕግ በኩል የሆኑት ወራሾች ከሆኑ እምነት ከንቱ ሆኗል፥ተስፋም ባዶ ሆኗል ማለት ነው።
15ሕግ ቁጣን ያመጣልና ሕግ ከሌለ አለመታዘዝም የለም።
16በዚህ ምክንያት በጸጋ ይሆን ዘንድ ይህ የሚደረገው በእምነት ነው። በመሆኑም ተስፋው ለዘሩ ሁሉ የተረጋገጠ ነው። ይህ ዘር ሕጉን የሚያውቁትን ብቻ ሳይሆን ደግሞም እንደ አብርሃም የሚያምኑትን ያካትታል።
17"ለሕዝቦች ሁሉ አባት አድርጌሃለሁ" ተብሎ ስለተጻፈ እርሱ የሁላችንም አባት ነው። አብርሃም ለሙታን ሕይወትን በሚሰጥና የሌሉትን ነገሮች ወደ መኖር በሚጠራ በታመነበት በእግዚአብሔር ፊት ነበረ።
18ውጫዊ ሁኔታዎች ሁሉ ተስፋ ሰጪዎች ባይሆኑም አብርሃም ስለ ወደፊቱ ሳይጠራጠር በእግዚአብሔር ታመነ። እንዲሁም "ዘርህ እንዲህ ይበዛል" ተብሎ እንደተነገረለት የብዙ ሕዝብ አባት ሆነ።
19በእምነት ደካማ አልነበረም። አብርሃም በመቶ አመቱ ገደማ የራሱን ሰውነትና የሣራም ማህጸን ምውት መሆኑን ተገነዘበ።
20ነገር ግን አብርሃም ከእግዚአብሔር ተስፋ የተነሣ በእምነት ዕጦት አላመነታም። ከዚህ ይልቅ በእምነት በረታ፥ ለእግዚአብሔርም ምስጋናን ሰጠ።
21እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ሊፈጽመው ደግሞ እንደሚችል በጥብቅ ተረዳ።
22ስለዚህ ይህም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።
23ተቆጠረለት የባለው ለእርሱ ጥቅም ብቻ የተጻፈ አይደለም።
24ጌታችን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው ለምናምን ለእኛም ደግሞ ይቆጠርልን ዘንድ ተጽፏል።
25እርሱም ስለ መተላለፋችን ተላልፎ የተሰጠውና እኛን ለማጽደቅ ከሙታን የተነሣው ነው።