1እንግዲህ የአይሁዳዊ ብልጫው ምንድነው? የመገረዝስ ጥቅሙ ምንድነው?
2በሁሉም አቅጣጫ ብልጫው ታላቅ ነው። አስቀድሞ ክእግዚአብሔር ዘንድ መገለጥ በአደራ የተሰጠው ለአይሁድ ነበር።
3አንዳንድ አይሁድ ባያምኑስ? ያለማመናቸው የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያስቀረዋልን?
4በምንም ዓይነት አያስቀረውም፤ ይልቁንም ሰው ሁሉ ውሸተኛ ቢሆንም እንኳ እግዚአብሔር እውነተኛ ነው። "በቃልህ ጸድቅ ሆነህ ትገኝ ዘንድ፥ ወደ ፍርድ በመጣህ ጊዜም ትረታ ዘንድ" ተብሎ ተጽፏልና።
5የእኛ አመጻ የእግዚአብሔርን ጽድቅ የሚያሳይ ከሆነ ግን ምን ማለት እንችላለን? እግዚአብሔር ቁጣውን በሚያመጣበት ጊዜ አመጸኛ አይደለም፥ ነወይ? ። ይህንን የምለው እንደ ሰው አስተሳሰብ ነው።
6በፍጹም አይደለም። እንዲህ ከሆነማ እግዚአብሔር እንዴት በዓለም ላይ ይፈርዳል?
7ነገር ግን የእግዚአብሔር እውነት በእኔ ውሸት አማካይነት ለእርሱ ብዙ ምስጋና ካመጣ ለምን አሁንም እንደ ኃጢአተኛ ይፈረድብኛል?
8"መልካም እንዲመጣ ክፉን እናድርግ" ስለማለታችን በሐሰት እንዳስወሩብንና አንዳንዶችም እንዳመኑት ታዲያ ለምን አንልም? የሚደርስባቸው ፍርድ ትክክለኛ ነው።
9እንግዲህ ምን ይሁን? በዚህ ጉዳይ ራሳችንን ነጻ እያደረግን ነውን? በጭራሽ። አይሁድና ግሪኮች ሁሉም ከኃጢአት በታች ስለመሆናቸው አስቀድመን ወንጅለናቸዋልና።
10እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ "አንድም እንኳን ጻድቅ የለም።
11አንድ እንኳን የሚያስተውል የለም። እግዚአብሔርን የሚፈልግ አንድም የለም።
12ሁሉም ተሳስተዋል። በአንድ ላይ የማይጠቅሙ ሆነዋል። መልካም የሚያደርግ የለም፥አንድም እንኳን የለም።
13ጉሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው። ምላሳቸው አታሏል። የእባብ መርዝ በከንፈሮቻቸው ሥር አለ።
14አፋቸው እርግማንና መራራነትን ተሞልቷል።
15እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው።
16በመንገዶቻቸው ላይ ጥፋትና መከራ አለ።
17እነዚህ ሰዎች የሰላምን መንገድ አላወቁትም።
18በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም።"
19ሕጉ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንደሆነ እናውቃለን። ይህም አፍ ሁሉ እንዲዘጋና መላው ዓለም ለእግዚአብሔር መልስ እንዲሰጥ ነው።
20ይህ የሆነበት ምክንያት ሥጋን የለበሰ ሁሉ ሕግን በመፈጸም በእግዚአብሔር ዓይን ስለማይጸድቅ ነው። ኃጢአት የሚታወቀው በሕግ አማካይነት ነውና።
21አሁን ግን የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጧል። ልዩነት ሳይደረግ
22በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የእግዚአብሔር ጽድቅ ለሚያምኑ ሁሉ ይሆንላቸው ዘንድ በሕግና በነቢያት የተመሰከረ ነው።
23ሁሉም ኃጢአትን ሠርተዋል፥ከእግዚአብሔር ክብርም ጎድለዋል።
24በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በተደረገው ቤዛነት በነጻ በጸጋው ይጸድቃሉ።
25በደሙ በማመን የኃጢአት ማስተሰሪያ ይገኝ ዘንድ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ሰጥቷልና። በትዕግስቱ የቀደመውን ኃጢአት ስለመተዉ ለጽድቁ ማረጋገጫ እንዲሆን ክርስቶስን መስዋዕት አድርጎ
26አቀረበው። በዚህ በአሁኑ ዘመን የእርሱ ጽድቅ እንዲታይ ይህ ሁሉ ሆነ። እንዲህም የሆነው እርሱ ጻድቅ መሆኑንና በኢየሱስ የሚያምነውን ሁሉ የሚያጸድቅ ራሱ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው።
27እንግዲህ ትምክህት ወዴት አለ? እርሱ ተወግዷል። ምን ላይ ተመሥርቶ? በሥራ ላይ ነውን? አይደለም፥በእምነት ላይ እንጂ።
28ስለዚህ ማንኛውም ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት ይጸድቃል እንላለን።
29ወይስ እግዚአብሔር የአይሁድ አምላክ ብቻ ነውን? የአሕዛብስ አምላክ አይደለምን? አዎን፥የአሕዛብም ደግሞ ነው።
30እግዚአብሔር አንድ ከሆነ የተገረዙትንም ሆነ ያልተገረዙትን ስለ እምነታቸው ያጸድቃቸዋል።
31እንግዲህ ሕግን በእምነት እንሽራለንን? እንዲህስ አይሁን። ይልቁንም ሕግን እናጸናለን።