1በእምነት ደካማ የሆነውን በጥያቄዎቹ ላይ በመፍረድ ሳይሆን በፍቅር ተቀበሉት።
2አንዳንዱ ማንኛውንም ነገር በእምነት ይበላል፥በእምነቱ ደካማ የሆነው ደግሞ አትክልት ብቻ ይበላል።
3ስለዚህ ማንኛውንም ዓይነት ምግብ የሚበላው የማይበላውን አይናቀው። የማይበላውም በሚበላው ላይ አይፍረድ። ምክንያቱም እግዚአብሔር ተቀብሎታል።
4በሌላው አገልጋይ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ? በገዛ ጌታው ፊት ወይ ይቆማል አሊያም ይወድቃል። ነገር ግን ጌታ ሊያቆመው ይችላልና ይቆማል።
5አንደኛው አንዱን ቀን ከሌላው ቀን የሚበልጥ አድርጎ ይቆጥራል። ሌላው ደግሞ ሁሉም ቀናት አንድ ናቸው ብሎ ያምናል። እያንዳንዱ ሰው የራሱ መረዳት ይኑረው።
6ቀንን የሚያከብር ለእግዚአብሔር ብሎ ያከብራል፥ የሚበላውም እግዚአብሔርን ያመሰግናልና ለእግዚአብሔር ብሎ ይበላል። የማይበላውም ራሱን ከመብላት ያቅባል። እርሱም እግዚእብሔርን ያመሰግናል።
7ምክንያቱም ከእኛ ማንም ለራሱ የሚኖር ወይም የሚሞት የለም።
8ብንኖር ለጌታ እንኖራልንና ብንሞትም ለጌታ እንሞታለንና። እንግዲያውስ ብንኖርም ብንሞትም የጌታ ነን።
9ምክንያቱም በሙታንና በህያዋን ላይ ጌታ ይሆን ዘንድ ለዚህ ዓላማ ክርስቶስ ሞቷል ደግሞም ህያው ሆኗል።
10ግን አንተ በወንድምህ ላይ ለምን ትፈርዳለህ? አንተስ ወንድምህን ለምን ትንቃለህ? ሁላችንም በእግዚአብሔር የፍርድ ዙፋን ፊት እንቆማለን።
11ምክንያቱም «እኔ ህያው ነኝና ጉልበት ሁሉ በፊቴ ይንበረከካል ምላስም ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናል» ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፏል።
12ስለዚህም እያንዳንዳችን ስለ ስራችን በእግዚአብሔር ፊት መልስ እንሰጣለን።
13ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ አንዳችን በሌላችን ላይ አንፍረድ በዚያ ፋንታ ማንም በወንድሙ ፊት መሰናክል ወይም ወጥመድ እንዳያስቀምጥ እንወስን።
14ምንም ነገር በራሱ ርኩስ እንዳልሆነ በጌታ በኢየሱስ አውቃለሁ ተረድቻለሁም። ማንኛውም ነገር ርኩስ ነው ብሎ ለሚያስብ ለእርሱ ብቻ ያ ነገር እርኩስ ነው።
15በምግብ ጉዳይ ወንድምህን የምታሰናክል ከሆነ አንተ በፍቅር እየተመላለስክ አይደለም። ስለምግብህ ብለህ ክርስቶስ የሞተለትን ሰው አታጥፋ።
16ስለዚህ መልካም ስራዎቻችሁን ለሰዎች መቀለጃ አታድርጉ።
17ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንግሥት በመንፈስ ቅዱስ የሚሆን ጽድቅ፥ ሠላምና ደስታ እንጂ የመብልና የመጠጥ ጉዳይ አይደለም።
18ክርስቶስ እንዲህ ባል ሁኔታ የሚያገለግለውን እግዚአብሔር ይቀበለዋል በሰዎችም ይመሰገናል።
19ስለዚህ ሠላም የሚገኝበትንና እርስበእርሳችን የምንተናነጽባቸውን ነገሮች እንፈልግ።
20በምግብ ምክንያት የእግዚአብሔርን ሥራ አታበላሹ። በእርግጥም ሁሉ ነገር ንጹህ ነው፥ ነገር ግን እየተጠራጠረ ለሚበላ ለዚያ ሰው ክፉ ነው፣ እንዲሰናከልም ያደርገዋል።
21ወንድምህን የሚጎዳ ከሆነ ሥጋ ባትበላም ወይን ባትጠጣም ወይም ምንም ባታደርግ መልካም ነው።
22አንተ በግልህ ያለህ መረዳት ባንተና በእግዚአብሔር መሀል ይቅር። አምኖ የተቀበለውን ነገር በማድረጉ ራሱን የማይወቅስ የተባረከ ነው።
23እየተጠራጠረ የሚበላ ግን በእምነት ስላልሆነ ይፈረድበታል። ምክንያቱም ያለ እምነት የሆነ ነገር ሁሉ ኃጢአት ነው።