1ከእግዚአብሔር ካልተሰጠ በቀር ሥልጣን የለምና ሰው ሁሉ ለመንግስት ባለሥልጣናት ይገዛ። አሁን በሥልጣን ላይ ያለውም የተሾመው በእግዚአብሔር ነው።
2ስለዚህም ይህን ሥልጣን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ይቃወማል፥ የሚቃወሙትም ሁሉ በራሳችው ላይ ፍርድን ያመጣሉ።
3ምክንያቱም ገዢዎች ክፉ ለሚያደርጉ እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉም። ባለሥልጣንን አለመፍራት ትፈልጋለህ? መልካምን አድርግ ከእርሱ ሽልማትን ታገኛለህ።
4ለመልካም ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። ክፉ የምታደርግ ከሆነ ግን ያለምክንያት ሠይፍ አልታጠቀምና ልትፈራ ይገባሀል። ምክንያቱም ክፉ የሚያደርገውን በቁጣ የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው።
5ስለዚህ ስለ ቁጣው ብለህ ብቻ ሳይሆን ስለህሊናህ ብለህ ልትገዛ ይገባሀል።
6በዚህ ምክንያት ግብርም ትከፍላላችሁ። ምክንያቱም ባለሥልጣናት ይህንን ጉዳይ ያለመታከት የሚቆጣጠሩ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው።
7ለእያንዳንዱ የሚገባውን ስጡ፥ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ አክብሮት ለሚገባው አክብሮትን ስጡ።
8እርስ በእርስ ከመዋደድ በቀር የማንም ዕዳ አይኑርባችሁ። ምክንያቱም ባልንጀራውን የሚወድ ህግን ፈጽሟል።
9ምክንያቱም «አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ አትመኝ» የሚሉትና ሌሎቹም ትዕዛዛት «ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ» በሚለው ትዕዛዝ ተጠቃለዋል።
10ፍቅር ያለው ባልንጀራውን አይጎዳም። ስለዚህ ፍቅር የህጉ ፍጻሜ ነው።
11በዚህም ምክንያት ከእንቅልፍ የምትነቁበት እንደደረስ ታውቃላችሁ። መዳናችን መጀመሪያ ካመንበት ጊዜ ይልቅ ቅርብ ነው።
12ሌሊቱ እያለፈ ቀኑም እየቀረበ ነው። ስለዚህ የጨለማን ሥራ ጥለን የብርሀንን የጦር ዕቃ እንልበስ።
13ቅጥ ባጣ ፈንጠዝያና በስካር ሳይሆን በቀን እንደሚመላለስ ሰው በተገቢው ሁኔታ እንመላለስ። በዝሙት ወይም በማይገታ ክፉ ምኞት፥ በጭቅጭቅና በቅናት አንመላለስ ።
14ይልቁኑ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት ለሥጋችሁና ለክፉ ምኞቱም ዕድል አትስጡ።