1ከዚህ በኋላ አራት መላእክት በአራቱም የምድር ማዕዘን ቆመው አየሁ፤ እነርሱም በምድር ቢሆን በባሕር ላይ ወይም በማንኛውም ዛፍ ላይ ፈጽሞ ነፋስ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳትን አጥብቀው ይከለክሉ ነበር።
2የሕያው አምላክ ማኅተም የያዘ ሌላ መልአክ ከምስራቅ ሲመጣ አየሁ። እርሱም ምድርንና ባሕርን ይጎዱ ዘንድ ሥልጣን ወደ ተሰጣቸው ወደ አራቱ መላእክት በታላቅ ድምፅ እየጮኽ፥
3«በአምላካችን አገልጋዮች ግምባር ላይ ማኅተም እስክናደርግ ድረስ ምድርንም ሆነ ባሕርን ወይም ዛፎችን እንዳትጎዱ» አለ።
4ከእስራኤል ሕዝብ ነገድ ሁሉ የታተሙት ሰዎች ቁጥር አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ እንደ ሆነ ሰማሁ።
5ከይሁዳ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ፥ከሮቤል ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ፥ከጋድ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥
6ከአሴር ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከንፍታሌም ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ፥ከምናሴ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ
7ከስምዖን ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ፥ከሌዊ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ከይሳኮር ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥
8ከዛብሎን ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ከዮሴፍ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ከብንያም ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ።
9ከዚህ በኋላ ከሕዝብ፥ከነገድ፥ከወገንና ከቋንቋ ሁሉ የመጡ ቁጥራቸው ማንም ሊቆጥረው የማይችል አጅግ ብዙ ሕዝብ ነጭ ልብስ ለብሰው፥ በእጃቸውም የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመው አየሁ።
10በታላቅ ድምፅም «ማዳን፥ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው የአምላካችንና የበጉ ነው!» እያሉ ይጮኹ ነበር።
11መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑ እና በሽማግሌዎች ዙሪያ እንዲሁም በአራቱ ሕያዋን ፍጡራን ዙሪያ ቆመው ነበር፤እነርሱም በመሬት ላይ ወድቀው በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር እየሰገዱ፥
12«አሜን! ውዳሴ፥ ክብር፥ጥበብ፥ምስጋና፥ኀይልና ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ለአምላካችን ይሁን፤አሜን» ይሉ ነበር።
13ከዚያም በኋላ ከሽማግሌዎች አንዱ፥«እነዚህ ነጭ ልብስ የለበሱ እነማናቸው ከየትስ የመጡ ናቸው?» በማለት ጠየቀኝ፤
14እኔም «ጌታ ሆይ፥አንተ ታውቃለህ» አልሁት። እርሱም እንዲህ አለኝ፤«እነዚህ በታላቁ መከራ ውስጥ አልፈው የመጡ ናቸው፤ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው በማንጻት ነጭ አድርገዋል።
15ክዚህም የተነሳ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት መሆን ችለዋል፤ እርሱንም በመቅደሱ ውስጥ ቀንና ሌሊት ያመልኩታል። በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው ድንኳኑን በእነርሱ ላይ ይዘረጋል።
16እነርሱም ከእንግዲህ አይራቡም፤አይጠሙምም። ፀሐይ አያቃጥላቸውም፤ ሙቀትም አያሰቃያቸውም።
17ምክንያቱም በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናል፤ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭ ይመራቸዋል፤እግዚአብሔር እንባንም ሁሉ ከዐይኖቻቸው ያብሳል።»