1ከዚህ በኋላ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ ምክንያቱም የመጀመሪያው ሰማይና የመጀመሪያው ምድር አልፈው ነበር፤ ባሕርም ከእንግዲህ አልተገኘም።
2ቅድስቲቱ ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንዳጌጠች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ።
3ከዙፋኑም እንዲህ የሚል ታላዝ ድምፅ ሰማሁ፣ “እነሆ የእግዚአብሔር መኖሪያ ከሰዎች ጋር ነው፤ ከእነርሱ ጋር ይኖራል። እነርሱ ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል።
4እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ሞት፣ ወይም ሐዘን፣ ወይም ለቅሶ ወይም ሕመም አይኖርም። ምክንያቱም የቀድሞ ነገሮች አልፈዋል።
5በዙፋኑ የተቀመጠው፣ “እነሆ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” አለ። “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛ ስለሆኑ ጻፍ” አለ።
6ለእኔም እንዲህ አለኝ፤”እነዚህ ሁሉ ተፈጽመዋል እኔ አልፋና ዖሜጋ፣ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ነኝ። ለተጠማ ሰው ከሕይወት ውሃ ምንጭ እንዲጠጣ ያለ ዋጋ እሰጣለሁ።
7ድል የነሣ እነዚህን ነገሮች ይወርሳል፤ አምላኩ እሆናለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል።
8ነገር ግን የፈሪዎች፣ የእምነተ ቢሶች፣ የርኩሶች፣ የነፍስ ገዳዮች፣ የአመንዝራዎች፣ የሟርተኞች፣ የጦዖት አምላኪዎችና የሐሰተኞኦች ቦታቸው በዲን በሚቃጠለው እሳት ባሕር ውስጥ ይሆናል። ይህም ሁለተኛው ሞት ነው።
9የመጨረሻዎቹ ሰባት መቅሠፍቶች የሞሉበትን ሰባት ድዋዎች ከያዙት ሰባት መላእክት አንዱ ወደ እኔ መጥቶ፣ “ወደዚህ ና፣ የበጉን ሚስት ሙሽራዋን አሳይሃለሁ” አለኝ።
10ከዚያም ወደ አንድ ታላቅና ከፍ ወዳለ ተራራ በመንፈስ ወሰደኝና ቅዱሳቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ።
11ኢየሩሳሌም የእግዚአብሔር ክብር ነበራት፤ የብርሃንዋ ፀዳል እጅግ እንደከበረ ድንጋይ፣ እንደ አያሰጲድ ድንጋይ ጥርት ያለ ነበር።
12አሥራ ሁለት በሮች ያሉት በጣም ታላቅ ረጅም ግምብ ነበራት በየበሮቹ አሥራ ሁለት መላእክት ነበሩ። በእነርሱም ላይ የአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ልጆች ስሞች ተጽፈው ነበር።
13በምሥራቅ ሦስት በሮች፣ በሰሜን ሦስት በሮች፣ በደቡብ ሦስት በሮች፣ በምዕራብ ሦስት በሮች ነበሩ።
14የከተማዋ ግምብ አሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩት፤ በእነርሱም ላይ የአሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር።
15ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ከተማዋን፣ በሮቹንና ቅጥሮቹን የሚለካበት የወርቅ ዘንግ ነበረው።
16ከተማዋ አራት ማእዘን ነበረች፤ ርዝመትና ስፋቱ ዕኩል ነበር። በመለኪያ ዘንጉ ሲለካ ርዝመቱ 12,000 ምዕራፍ ሆነ (ርዝመቱ፣ ስፋቱና ከፍታዋ ዕኩል ነበር)።
17ቅጥሯን ስለካ ስፋቱ በሰው መለኪያ (ይህም የመላእክት መለኪያም ነው) 144 ክንድ ሆነ
18ቅጥሩ ከኢያሰጲድ፣ ከተማዋም እንደ መስተዋት በጠራ ንጹሕ ወርቅ የተሠራች ነበረች።
19የቅጥሩ መሠረቶች በከበሩ ድንጋዮች ያጌጡ ነበር። የመጀመሪያው ኢያሰጲድ፣ ሁለተኛው ሶንፔር፣ ሦስተኛው ኬልቄዶን፣ አራተኛው መረግድ
20አምስተኛው ሰርደንክስ፣ ስድስተኛው ሰርድዮን፣ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፣ ስምንተኛው ቢረሌ፣ ዘጠነኛው ወራውሬ፣ አሥረኛው ክርስጵራስስ፣ አሥራ አንደኛው ያክንት፣ አሥራ ሁለተኛው አሜቴስ ቲኖስ ነበረ።
21አሥራ ሁለቱም በሮች፣ አሥራ ሁለት ዕንቁዎች ነበሩ፤ እያንዳንዱ በር ከአንድ ዕንቁ የተሠራ ነበር። የየከተማዋ መንገዶች ጥርት እንዳለ መስተዋት ንጽሕ ወርቅ ነበሩ።
22በከተማዋ ምንም መቅደስ አላየሁም፤ ምክንያቱም ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደሷ ነበሩ።
23የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራለት ከተማዋ የፀሐይ ወይም የጨረቃ ብርሃን አልነበራትም፤ ምክንያቱም በጉ ራሱ ብርሃንዋ ነው።
24ሕዝቦችም በዚያች ከተማ ብርሃን ይመላለሳሉ። የምድር ነገሥታት ክብራቸውን ወደ እርሷ ያመጣሉ።
25በሮቿ በቀን አይዘጉም፤ በዚያ ሌሊት የለም።
26የመንግሥታትን ግርማና ክብር ወደ እርሷ ያመጣሉ
27ርኩስ ነገር በፍጹም አይገባባትም። ጸያፍ ወይም አታላይ ወደዚያ አይገባም፤ ወደዚያ የሚገቡት ስሞቻቸው በበጉ የሕይወት መጽሐፍ የተጻፈ ብቻ ናቸው።