1ሰባቱን መላእክት፣ “ሂዱና ሰባቱን የእግዚአብሔርን ቁጣ ጽዋዎች ምድር ላይ አፍስሱ” የሚል ታላቅ ድምፅ ከመቅደሱ ሲወጣ ሰማሁ።
2የመጀመሪያው መልአክ ጽዋውን ምድር ላይ አፈሰሰ፤ የአውሬው ምልክት ባላቸውና ለምስሉ በሰገዱት አስከፊና የሚያሠቃይ ቁስል ወጣባቸው።
3ሁለተኛው መልአክ ጽዋውን ባሕር ላይ አፈሰሰ፤ ባሕሩ እንደ ሞተ ሰው ደም ሆነ፤ ባሕር ውስጥ የነበረ ሕያው ፍጡር ሁሉ ሞተ።
4ሦስተኛው መልአክ ጽዋውን ወንዞችና የውሃ ምንጮች ላይ አፈሰሰ እነርሱም ደም ሆኑ።
5የውሃውም መልአክ፣ “ያለህና የነበርህ ቅዱስ ጌታ እንዲህ ስለ ፈረድህ ትክክል ነህ፣
6ምክንያቱም የቅዱሳንህና የነበያትን ደም ስላፈሰሱ፣ ደም አጠጣሃቸው፤ ይህም የሚገባቸው ነው” ሲል ሰማሁ።
7ከመሠዊያውም፣ “አዎን፣ ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ፍርድህ እውነትና ትክክል ነው” የሚል ድምፅ ወጣ።
8አራተኛው መልአክ ጽዋውን ፀሐይ ላይ አፈሰሰ፤ ለእርሷም ሰዎችን በግለትዋ የማቃጠል ሥልጣን ተሰጣት።
9ሰዎች በከባድ ሙቀቷ ተቃጠሉ፤ በእነዚህ መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔር ስም ሰደቡ። ንሰሐ አልገቡም፤ ክብርም አልሰጡትም።
10አምስተኛው መልአክ ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ የአውሬውም መንግሥት በጨለማ ተዋጠ። ከሥቃያቸውም የተነሣ ምላሳቸውን ያኝኩ ነበር።
11ከሥቃያቸውና ከደረሰባቸው ቁስል የተነሣ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ፤ ያም ሆኖ ግን ስላደረጉት ክፉ ሥራ ንስሐ ለመግባት ፈቃደኞች አልሆኑም።
12ስድስተኛው መልአክ ጽዋውን ታላቁ ወንዝ ኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከምሥራቅ ለመጡ ነገሥታት መንገድ ለማዘጋጀት የወንዙ ውሃ ደረቀ።
13ከዘንዶው አፍና ከአውሬው አፍ እንዲሁም ከሐስተኛው ነቢይ አፍ እንቁራሪት የሚመስሉ ሦስት ርኩሳን መናፍስት ስወጡ አየሁ።
14እነዚህ ተአምራዊ ምልክቶች የሚያደርጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸው። ሁሉን በሚገዛ አምላክ ታላቅ ቀን ለሚደረገው ጦርነት የዓለም መንግሥታችን ሁሉ ለመሰብሰብ ወደ ወጥተው ሄዱ።
15“ልብ በሉ! እኔ እንደ ሌባ እመጣለሁ! ራቁቱን እንዳይገኝና ሰዎችም ሐፍረቱን እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ የተባረከ ነው።”
16መናፍስቱ ነገሥታቱን ሰብስበው በዕብራይስጥ አርማጌደን ወደሚባል ቦታ አመጧቸው።
17ሰባተኛው መልአክ ጽዋውን አየር ላይ አፈሰሰ። በዚያን ጊዜ፣ “ተፈጸመ!” የሚል ታላቅ ድምፅ ከመቅደሱና ከዙፋኑ ወጣ።
18ከዚያም የመብረቅ ብልጥታ፣ ሁካታ ነጎድጓድና ከባድ የመሬት መናወጥ ሆነ፤ የዚያ ዓይነት የምድር ነውጥ የሰው ልጅ ምድር ላይ መኖር ከጀመረ አንሥቶ ሆኖ የማያውቅ እጅግ ከባድ ነበር።
19ታላቂቷ ከተማ ለሦስት ተከፈለች፤ የሕዝቦች ከተሞችም ተደመሰሱ። እግዚአብሔር ታላቂቱ ባቢሎንን አስታወሰ፤ ለዚያች ከተማም የብርቱ ቁጣው ወይን ጠጅ የሞላበት ጽዋ እንድትጠጣ ሰጣት።
20ደሴቶች ሁሉ ጠፋ፤ ተራሮችም በቦታቸው አልተገኙም።
21አንድ ታለንት የሚመዝን የበረዶ ድንጋይ ከሰማይ ወርዶ ሰዎች ላይ ወደቀ፤ መቅሠፍቱ እጅግ አሰቃቂ ከመሆኑ የተነሣ ሰዎች ስለ በረዶው ድንጋይ እግዚአብሔርን ተራገሙ።