1ከዚያም ለመለኪያ የሚያገለግል አንድ ረዥም ዘንግ ተሰጠኝ፤እንዲህም ተባልሁ፣«ተነሥተህ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፥ መሰዊያውንና በዚያ የሚያመለኩትንም ቍጠር።
2ከቤተመቅደሱ ውጭ ያለውን አደባባይ ግን ተወው፤ እርሱ ለአሕዛብ የተሰጠ ስለ ሆነ አትለካው፥አሕዛብ ቅድስቲቱን ከተማ አርባ ሁለት ወራት ይረግጧታል።
3ሁለቱ ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ለ1260 ቀን ትንቢት እንዲናገሩ ሥልጣን እሰጣቸዋለሁ።»
4እነዚህም በምድር ጌታ ፊት የቆሙ ሁለቱ የወይራ ዛፎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው፤
5ማንም እነርሱን ሊጎዳ ቢፈልግ እሳት ከአፋቸው ወጥቶ ጠላቶቻቸውን ይበላል፤ እነርሱን ሊጎዳ የሚፈልግ ሁሉ የሚሞተው በዚህ ዐይነት ነው፥
6እነዚህ ምስክሮች ትንቢት በሚናገሩባቸው ቀናት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ለመዝጋት ሥልጣን አላቸው፥ እንዲሁም ውሆችን ወደ ደም ለመለወጥና በሚፈልጉበትም ጊዜ ሁሉ በማንኛውም ዓይነት መቅሰፍት ምድርን ለመምታት ሥልጣን አላቸው፡
7ምስክርነታቸውን በጨረሱ ጊዜ ከጥልቁ ጉድጛድ የሚወጣው አውሬ ከእነርሱ ጋር ይዋጋል፤ ያሸንፋቸዋል ይገድላቸውማል።
8ሬሳቸውም በምሳሌያዊ አጠራር ሰዶም ወይም ግብጽ ተብላ በምትጠራው በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይጋደማል፤ ከተማይቱም የእነርሱ ጌታ የተሰቀለባት ናት፤
9ከልዩ ልዩ ወገን፥ ነገድ፥ ከልዩ ልዩ ቋንቋና ሕዝብ የሆኑ ሰዎች ሶስት ቀን ተኩል ሬሳቸውን ይመለከታሉ፥ ሬሳቸውም እንዳይቀበር ይከለክላሉ።
10ሁለቱ ነቢያት የምድርን ሰዎች ሁሉ አስጨንቀው ስለ ነበር፣ በእነርሱ ሞት በምድር የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ደስ ይላቸዋል፤ በደስታም በዓል ያደርጋሉ፤ ስጦታም ይለዋወጣሉ።
11ነገር ግን ሦስት ቀን ተኩል ካለፈ በኋላ፣ የሕይወት እስትንፋስ ከእግዚአብሔር መጥቶ ወደ ሬሳዎቹ ይገባል፤ በእግራቸውም ይቆማሉ፤ የሚመለከቷቸውም ሰዎች ታላቅ ፍርሃት ይወድቅባቸዋል።
12ከዚህ በኋላ ሁለቱ ነቢያት፣ «ወደዚህ ውጡ» የሚል ታላቅ ድምጽ ከሰማይ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸውም እየተመለከቷቸው በደመና ወደ ሰማይ ወጡ።
13በዚያኑ ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የከተማይቱም አንድ ዐሥረኛ ወደመ። በምድር መናወጥም ምክንያት ሰባት ሺህ ሰዎች ሞቱ፤ ከሞት የተረፉትም እጅግ ፈሩ፤ለሰማይም አምላክ ክብርን ሰጡ።
14ሁለተኛው ወዮ አልፎአል፤ልብ በል! ሦስተኛው ወዮ ፈጥኖ ይመጣል።
15ሰባተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤በሰማይም«የዓለም መንግሥት የጌታ አምላካችንና የእርሱ ክርስቶስ ሆናለች፤ እርሱም ለዘላለም ይነግሣል» የሚል ታላቅ ድምጽ ሰማሁ።
16በእግዚአብሔርም ፊት በዙፋኖቻቸው ላይ የተቀመጡት ሃያ አራቱም ሽማግሌዎች በግምባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤
17እነርሱም እንዲህ አሉ፣«ያለህና የነበርህ፣ ሁሉን የምትችል፣ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ትልቁን ሥልጣንህን በእጅህ አድርገህ ስለ ነገሥህ እናመሰግንሃለን።
18አሕዛብ ተቆጡ፤ ነገር ግን የአንተም ቁጣ መጣ ።በሙታን ላይ የምትፈርድበት ዘመንም መጣ፤ለአገልጋዮችህ፣ ለነቢያት፣ ለቅዱሳን፣ ስምህንም ለሚያከብሩት ለታናናሾችና ለታላላቆች ሽልማታቸውን የምትሰጥበት ጊዜ እንዲሁም ምድርን ያጠፏትን የምታጠፋበት ጊዜ ደረሰ።»
19በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተከፈተ፤የእርሱም የቃል ኪዳን ታቦት በቤተ መቅደሱ ውስጥ ታየ። መብረቅ የመብረቅ ድምጽ፣ነጎድጓድም፣የምድር መናወጥና ታላቅም ማዕበል ሆነ።