1ከዚህ በኋላ ሌላ ብርቱ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። እርሱም ደመናን የለበሰ ነበር። በራሱም ዙሪያ ቀስተ ደመና ነበር። ፊቱ እንደ ፀሐይ እግሮቹ እንደ እሳት ዐምድ ነበሩ፤
2የተከፈተ ትንሽ ጥቅል መጽሐፍ በእጁ ይዞ ነበር፤ ቀኝ እግሩን በባህር ላይ ግራውንም በምድር ላይ አደረገ።
3ከዚያም እንደሚያገሳ አንበሳ በመሰለ ታላቅ ድምጽ ጮኸ፤ በጮኸ ጊዜ፣ ሰባቱም ነጎድጓዶች ድምፃቸውን አሰሙ ፤
4ሰባቱ ነድጓዶች በተናገሩ ድምፃቸውን ባሰሙ ጊዜ፣ እኔ ልጽፍ አሰብሁ። ነገር ግን «ሰባቱ ነጎድጓዶች የተናገሩትን በምስጢር ያዘው እንጂ አትጻፈው» የሚል ድምጽ ከሰማይ ሰማሁ።
5ከዚያም በባህርና በምድር ላይ ቆሞ ያየሁት መልአክ ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ አነሣና
6ዘላለም በሚኖረው ሰማይንና በእርሱ ያሉትን፣ ምድርንና በእርስዋ ያሉትን፣ ባህርንና በርስዋ ያሉትን በፈጠረው አምላክ ስም ማለ። እንዲህም አለ፤«ከእንግዲህ ወዲህ አይዘገይም
7ነገር ግን ሰባተኛው መልአክ መለከቱን በሚነፋበት ቀን ለአገልጋዮቹ ለነቢያት በገለጠላቸው መሰረት የእግዚአብሔር ምስጢር ይፈጸማል።»
8ከሰማይ የሰማሁት ድምጽ፣«በባህርና በምድር ላይ የቆመው መልአክ በእጁ የያዘውንና የተፈታውን ጥቅል መጽሐፍ ሂድና ውሰድ» ብሎ እንደገና ሲናገረኝ ሰማሁት»።
9ወደ መልእኩም ሄጄ «ትንሹን ጥቅል መጽሐፍ ስጠኝ?» አልሁት። እርሱም «ውሰድና ብላ በሆድህም ውስጥ መራራ ይሆናል፤ በአፍህ ግን እንደ ማር ይጣፍጣል»አለኝ።
10እኔም ትንሹን ጥቅል መጽሐፍ ከመልአኩ እጅ ወስጄ በላሁት፤ በአፌ እንደ ማር ጣፈጠ፤ ከበላሁት በኋላ ግን ሆዴ መራራ ሆነ።
11ከዚህም በኋላ «ስለብዙ ሕዝቦች፤ አገራት፤ ልዩ ልዩ ቋንቋ ስለሚናገሩ ሰዎችና ሰለ ነገሥታት እንደ ገና ትንቢት መናገር አለብህ» ተብሎ ተነገረኝ።