1በፍጹም ልቤ ያህዌን አመሰግናለሁ ስለ ድንቅ ሥራዎችህም እናገራለሁ፡፡
2በአንተ ደስ ይለኛል፤ ሐሤትም አደርጋለሁ ልዑል ሆይ፣ ለስምህ እዘምራለሁ!
3ጠላቶቼ ወደ ኋላ በተመለሱ ጊዜ ተሰነካክለው በፊትህ ይጠፋሉ፡፡
4በዙፋንህ ላይ ተቀምጠህ ጻድቅ ፈራጅ ነህ! የእኔን ጉዳይም ትፈርድልኛለህ፡፡
5ሕዝቦችን ገሠጽህ ክፉዎችን አጠፋህ ስማቸውን ከዘላለም እስከ ዘላለም ደመሰስህ፡፡
6ጠላቶች ለዘላለም ጠፍተዋል ከተሞቻቸውንም ገለባበጥሃቸው መታሰቢያቸውንም አጠፋህ፡፡
7እግዚአብሔር ግን ለዘላለም ዙፋኑ ላይ ነው ዙፋኑንም ለፍርድ አጽንቶአል፡፡
8ዓለምን በጽድቅ ይዳኛል ለሕዝቦችም በፍትሕ ይፈርዳል፡፡
9ያህዌ ለተጨቆኑት ዐምባ ነው፡፡ በመከራም ጊዜ መጠጊያ ይሆናቸዋል፡፡
10ስምህን የሚያውቁ በአንተ ይታመናሉ አንተ ያህዌ፣ የሚፈልጉህን አትተዋቸውም፡፡
11በጽዮን ለሚገዛ ለያህዌ ምስጋና ዘምሩ ድንቅ ሥራውን ለሕዝቦች ተናገሩ፡፡
12ደም ተበቃዩ አስቦአቸዋልና የጭቁኖችን ጩኸት አልዘነጋም፡፡
13ያህዌ ሆይ፣ ማረኝ በሚጠሉኝ የደረሰብኝን ጭቆና ተመልከት አንተ ከሞት አፋፍ ነጥቀህ አድነኝ፡፡
14ይህን ብታደርግልኝ፣ በጽዮን አደባባይ ምስጋናህን ሁሉ ለሕዝብ እናገራለሁ በማዳንህም ደስ እሰኛለሁ!
15ሕዝቦች ባዘጋጁት አዘቅት ሰጠሙ እግሮቻቸውም በሰወሩት ወጥመድ ተያዙ፡፡
16እግዚአብሔር በእውነተኛ ፍርዱ ታወቀ ክፉዎችም በእጃቸው ሥራ ተጠመዱ፡፡
17ክፉዎች ተመልሰው ወደ ሲኦል ይወርዳሉ፡፡ እግዚአብሔርን የሚዘነጉ ሰዎች ሁሉ ፍጻሜ ይኸው ነው፡፡
18ችግረኞች መቼም ቢሆን አይዘነጉም የድኾችም ተስፋ ከንቱ ሆኖ አይቀርም፡፡
19ያህዌ ሆይ ተነሥ፣ ሰውም አያይል ሕዝቦችም በፊት ይፈረድባቸው፡፡
20ያህዌ ሆይ፣ አስደንግጣቸው ሕዝቦች ሰዎች ብቻ መሆናቸውን ይወቁ፡፡ ሴላ