መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መጽሐፈ መዝሙር 89

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ስለ ያህዌ ምሕረት ለዘላለሙ እዘምራለሁ፡፡ ታማኝነትህንም ለሚመጣው ትውልድ እናገራለሁ፡፡
2ምሕረትህን ለዘላለም እንደምትመሠርት ታማኝነትህንም በሰማያት እንደምታጸና እናገራለሁና
3አንተም እንዲህ ብለሃል፣ «ከመረጥሁት ጋር ኪዳን አድርጌአለሁ፤ ለባርያዬ ለዳዊት ምዬአለሁ፡፡
4ዘርህን ለዘላለም አተክላለሁ ዙፋንህንም በትውልድ ዘመን ሁሉ አጸናለሁ፡፡» ሴላ
5ያህዌ ሆይ፣ ሰማያት ድንቅ ሥራህን ያመሰግናሉ ጽድቅህም በቅዱሳን ጉባኤ ይወደሳል፡፡
6በላይ በሰማያት ከያህዌ ጋር ማን ሊስተካከል ይችላል? ከአማልክት ልጆችስ መካከል እንደ ያህዌ ያለ ማን ነው?
7እርሱ በቅዱሳኑ ጉባኤ መካከል እጅግ የተፈራ ነው፤ በዙሪያው ካሉትም ሁሉ ታላቅና አስፈሪ ነው፡፡
8የሰራዊት ጌታ ያህዌ ሆይ፣ እንደ አንተ ያለ ኃያል ማነው? ታማኝነትህም ከቦሃል፡፡
9የባሕሩን ቁጣ በሥልጣንህ ታዝዛለህ ማዕበሉንም ጸጥ ታደርጋለህ፡፡
10አንተ ረዓብን ቀጥቅጠህ ገደልኸው በታላቁ ኃይልህ ጠላቶችህን በተንሃቸው፡፡
11ሰማያት የአንተ ናቸው ምድርም የአንተ ናት፡፡ አንተ ዓለምንና በውስጧ ያሉትን ሁሉ ፈጠርህ፡፡
12ሰሜኑን ደቡቡንም አንተ ፈጠርህ ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል፡፡
13አንተ ክንደ ብርቱ ነህ እጅህ ኃያል ናት፤ ቀኝ እጅህም ከፍ ከፍ ያለች ናት፡፡
14ጽድቅና ፍትሕ የዙፋንህ መሠረት ናቸው ምሕረትና ታማኝነት በፊት ይሄዳሉ፡፡
15ያህዌ ሆይ፣ በፊት ብርሃን የሚሄድ አንተንም የሚያመልክ ሕዝብ ቡሩክ ነው፡፡
16ቀኑን ሙሉ በስምህ ደስ ይላቸዋል በጽድቅህም ከፍ ከፍ ይላሉ፡፡
17ገናናው ኃይልህ ብርታት ይሰጣቸዋል በሞገስህም ድል ተቀዳጀን፡፡
18ጋሻችን የያህዌ ነው ንጉሣችንም የራሱ የእስራኤል ቅዱስ ነውና፡፡
19ከረጅም ጊዜ በፊት በራእይ ለሕዝብህ ተናገርህ እንዲህም አልህ፤ «ኃያሉን ሰው ሥልጣን አጐናጸፍሁ፤ ከሕዝብ መካከል እኔ የመረጥሁትን አስነሣሁ፡፡
20ባርያዬ ዳዊትን መረጥሁት በተቀደሰው ዘይቴም ቀባሁት
21እጄ ይደግፈዋል ክንዴም ያበረታዋል፡፡
22ጠላት አይረታውም ክፉ ሰውም አያሸንፈውም፡፡
23ጠላቶቹን በፊቱ አደቃለሁ፤ ባላንጣዎቹንም እገድላለሁ፡፡
24እውነቴና ታማኝነቴ ከእርሱ ጋር ይሆናል በስሜ ድል ይቀዳጃል፡፡
25እጁን በባሕሮች ቀኝ እጁንም በወንዞች ላይ አደርጋለሁ፡፡
26እርሱም፣ «አንተ አባቴ፣ አምላኬ የድነቴም ዐለት» ብሎ ይጠራኛል፡፡
27እኔም ደግሞ በኩሬ አደርገዋለሁ ከምድር ነገሥታትም ሁሉ በላይ ከፍ ይላል፡፡
28ምሕረቴንም ለዘላለም ለእርሱ እዘረጋለሁ ለእርሱ ጋር ያደረግሁትም ኪዳን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፡፡
29የዘር ሐረጉን ለዘላለም ዙፋኑንም በሰማያት ዕድሜ ልክ አጸናለሁ
30ልጆቹ ሕጌን ቢተው፣ ሥርዐቴን ባይጠብቁ፣
31ደንቤን ቢተላለፉ፣ ትእዛዞቼ ባያከብሩ፣
32ኃጢአታቸውን በበትር፣ በደላቸውንም በአለንጋ እቀጣለሁ፡፡
33ለእርሱ ያለኝ ፍቅር ግን አይቋረጥም ታማኝነቴንም አላጓድልበትም፡፡
34ኪዳኔን አላፈርስም ከአፌ የወጣውን አላጥፍም፡፡
35አንዴ በቅድስናዬ ምያለሁና ለዳዊት አልዋሽም፡፡
36ልጆቹ ለዘላለም ዙፋኑም በፀሐይ ዕድሜ ልክ ጸንቶ ይኖራል፡፡
37በሰማይ ታማኝ ምስክር ሆና እንደምትኖረው እንደ ጨረቃ እርሱም ለዘላለም ይመሠረታል፡፡ ሴላ
38አሁን ግን ናቅኸው፤ ጣልኸውም በቀባኸውም ንጉሥ ላይ ተቆጣህ፡፡
39ለባርያህ የገባኸውን ኪዳን አፈረስህ የክብር ዘውዱን መሬት ላይ ጣልህ፡፡
40ቅጥሮቹን ሁሉ አፈረስህ ምሽጉንም ደመሰስህ፡፡
41ዐላፊ አግዳሚ ሁሉ ዘረፈው ለጐረቤቶቹም መዘባበቻ ሆነ፡፡
42የጠላቶቹን ቀኝ እጅ ከፍ አደረግህ ባላንጣዎቹም ሁሉ ደስ አላቸው፡፡
43የሰይፉን ስለት አጠፍህ በጦርነትም ጊዜ አልረዳኸውም፡፡
44የክብሩን ውበት አጠፋህበት ዙፋኑንም መሬት ላይ ጣልህበት፡፡
45የወጣትነት ዘመኑን አሳጠርኸው ዕፍረትንም አከናነብኸው፡፡
46ያህዌ ሆይ፣ ይህ እስከ መቼ ነው? ራስህንስ ለዘላለም ትሰውራለህን? ቁጣህስ እንደ እሳት የሚነደው እስከ መቼ ነው?
47ዕድሜዬ ምን ያህል አጭር እንደ ሆነ አስብ፤ የሰውን ልጆች እንዲሁ ለከንቱ ፈጠርሃቸው!
48ሞትን ሳያይ ሕያው ሆኖ የሚኖር ማን ነው? ሕይወቱን ከሲኦል እጅ ማዳን የሚችል ማነው? ሴላ
49ጌታ ሆይ፣ በታማኝነትህ ለዳዊት የማልህለት የቀድሞ ምሕረትህ የታለ?
50ጌታ ሆይ፣ ባርያህ ላይ የደረሰውን ፌዝ የብዙ ሰዎችንም ስድብ እንደ ታቀፍሁ አስብ፡፡
51ያህዌ ሆይ፣ ጠላቶችህ የሚሳደቡትን፣ አንተ የቀባኸውን ሰው ርምጃ የነቀፉበትን ሁኔታ አስብ፡፡
52ያህዌ ለዘላለም ይባረክ፡፡ አሜን፣ አሜን
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።