1አዳኜ ያህዌ አምላክ ሆይ፤ ቀንና ሌሊት በፊትህ እጮኻለሁ፡፡
2እባክህ ጸሎቴን ስማ፤ ጩኸቴንም አድምጥ፡፡
3በመከራ ተሞልቻለሁና ነፍሴም ወደ ሲኦል ተቃርባለች፡፡
4ወደ መቃብር ከሚወርዱ ጋር ተቆጥሬአለሁ፤ ዐቅም አጣሁ፡፡
5በሙታን መካከል ፈጽሞ እንደ ተተዉ ሞተው መቃብር ውስጥ እንደ ተጋደሙ ከእንግዲህ ፈጽሞ እንደማታስታውሳቸውና ከእጅህ ወጥተው እንደ ተወገዱ ሆንሁ፡፡
6ጥልቁ አዘቅት ውስጥ ጣልኸኝ ጨለማ ጉድጓድ ውስጥ ከተትኸኝ፡፡
7ቁጣህ እጅግ ከብዶኛል ማዕበልህም ሁሉ አጥለቅልቆኛል፡፡
8ወዳጆቼን ሁሉ ከእኔ አራቅህ እንዲጸየፉኝም አደረግህ ዙሪያውን ተከብቤአለሁና ማምለጥ አልችልም፡፡
9ዐይኖቼ በሐዘን ፈዘዙ ያህዌ ሆይ፣ ቀኑን ሙሉ ወደ አንተ እጮኻለሁ እጆቼን ወደ አንተ ዘረጋሁ፡፡
10ለሙታን ተአምራት ታደርጋለህን? የሞቱትስ ተነሥተው ያመሰግኑሃልን? ሴላ
11ምሕረትህ መቃብር ውስጥ ታማኝነትህስ በሙታን ዓለም ይነገራልን?
12ድንቅ ሥራህ በጨለማ ስፍራ ጽድቅህስ በመረሳት ምድር ትቃወቃለችን?
13ያህዌ ሆይ፣ እኔ ግን ወደ አንተ እጮኻለሁ በጧትም ጸሎቴን ወደ ፊት አቀርባለሁ፡፡
14ያህዌ ሆይ፣ ለምን ትተወኛለህ? ፊትህንስ ከእኔ ለምን ትሰውራለህ?
15ከልጅነቴ ጀምሮ ችግረኛና ሞት አፋፍ ላይ ያለሁ ሰው ነበርሁ፤ ከማስደንገጥህ የተነሣ ተስፋ ቆርጫለሁ፡፡
16ቁጣህ እኔ ላይ ተከነበለ መዓትህም አጠፋኝ፡፡
17ቀኑን ሙሉ እንደ ጐርፍ ከበቡኝ ዙሪያውን አጥረው ያዙኝ፡፡፡
18ወዳጆቼንና የሚቀርቡኝን ሰዎች ሁሉ ከእኔ አራቅህ ጓደኛዬ ጨለማ ብቻ ሆኖ ቀረ፡፡