1ያህዌ ሆይ፣ እኔ ድኻና ምስኪን ነኝና እባክህ ስማኝ መልስልኝም፡፡
2እኔ ለአንተ ታማኝ ስለሆንሁ ጠብቀኝ አምላኬ ሆይ፤ በአንተ የታመነውን ባርያህን አድነው፡፡
3ጌታ ሆይ፣ ቀኑን ሙሉ ወደ አንተ እጮኻለሁና እባክህ ማረኝ፡፡
4ጌታ ሆይ፣ ወደ አንተ እጸልያለሁና ባርያህን ደስ አሰኘው፡፡
5ጌታ ሆይ፣ አንተ መልካምና ይቅር ባይ ነህ ለሚጠሩህ ሁሉ ምሕረትህ ወሰን የለውም፡፡
6ያህዌ ሆይ ጸሎቴን አድምጥ የልመናዬንም ጩኸት ስማ፡፡
7አንተ ስለምትመልስልኝ በመከራዬ ቀን ወደ አንተ እጣራለሁ፡፡
8ጌታ ሆይ፣ ከአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ የለም፡፡ ከአንተ ሥራ ጋር የሚወዳደር ሥራ የለም፡፡
9ጌታ ሆይ፣ የሠራሃቸው ሕዝቦች ሁሉ መጥተው በፊት ይሰግዳሉ፡፡ ስምህን ያከብራሉ፡፡
10አንተ ታላቅ ነህና ተአምራትን ታደርጋለህ አንተ ብቻህን አምላክ ነህ፡፡
11ያህዌ ሆይ፣ መንገድህን አስተምረን፤ እኔም በእውነትህ እሄዳለሁ፡፡ ባልተከፋፈለ ልብም እንዳከብርህ አድርገኝ፡፡
12ጌታ አምላኬ ሆይ፣ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ ስምህንም ለዘላለም አከብራለሁ
13ለእኔ የምታሳየው ዘላለማዊው ፍቅርህ እጅግ ታላቅ ነው፡፡ ነፍሴንም ከጥልቁ ሲኦል አወጣሃት፡፡
14አምላክ ሆይ፣ እብሪተኞች ተነሥተውብኛል የክፉዎች ጉባኤ ነፍሴን ይፈልጓታል፡፡ አንተንም ከምንም አልቆጠሩም፡፡
15አንተ ግን ጌታ ሆይ፣ መሐሪና ርኅሩኅ አምላክ ነህ ለቁጣ የዘገየህ፣ ምህረትህና ታማኝነትህ የበዛ ነው፡፡
16ወደ እኔ ተመለስ ማረኝም ለባሪያህ ብርታትህን ስጥ የሴት ባሪያህንም ልጅ አድን፡፡
17የሞገስህን ምልክት አሳየኝ አንተ ያህዌ ረድተኸኛልና አጽናንተኸኛልምና የሚጠሉኝ ይህን አይተው ያፍራሉ፡፡