መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መጽሐፈ መዝሙር 78

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ሕዝቤ ሆይ፣ ትምህርቴን ሰሙ የአፌንም ቃል አድምጡ፡፡
2አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ ከጥንት ጀምሮ የተሰወረውን ምስጢር እገልጣለሁ፡፡
3ይህም የሰማነውና ያወቅነው አባቶቻችንም የነገሩን ነው፡፡
4እኛም ከልጆቻቸው አንደብቀውም ስለ እግዚአብሔር ኃይል ስላከናወናቸውም ታላላቅ ሥራዎችና ስላደረጋቸው ድንቅ ነገሮች ለተከታዩ ትውልድ እንገራለን፡፡
5ለያዕቆብ ሥርዐትን መሠረተ ለእስራኤልም ሕግን ደነገገ፡፡ ይህንንም ለሚቀጥለው ትውልድ እንዲያስተምሩ አባቶቻችንን አዘዘ፡፡
6ይህም የሚመጣው ትውልድ ሥርዐቱን እንዲያውቅ እነርሱም በተራቸው ለልጆቻቸው ገና ለሚወለዱትም እንዲነግሩ ነው፡፡
7እነርሱም በእግዚአብሔር ይታመኑ የእግዚአብሔርን ሥራ አይረሱም ትእዛዞቹንም ይጠብቃሉ፡፡
8እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው እልኸኛና ዐመፀኛ አይሆኑም፤ እነርሱ እግዚአብሔርን በማመን አልጸኑም ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆነው አልኖሩም፡፡
9የኤፍሬም ሰዎች የታጠቁ ቀስተኖች ቢሆኑም በጦርነት ቀን ወደ ኃላ ተመለሱ፡፡
10የእግዚአብሔርን ኪዳን አልጠበቁም፣ በሕጉ መሠረት መኖርም አልፈለጉም፡፡
11ሥራዎቹን ረሱ ያሳያቸውንም ድንቆች ዘነጉ፡፡
12በግብፅ ምድር፣ በዞዓር ምድር በአባቶቻቸው ፊት ያደረጋቸውን ድንቆች ዘነጋ፡፡
13ባሕሩን ከፍሎ አሻገራቸው ውሃውንም እንደ ግድግዳ አቆመው፡፡
14ቀን በደመና፣ ሌሊቱንም ሁሉ በእሳት ብርሃን መራቸው፡፡
15በምድረ በዳ ዐለቱን ሰነጠቀ እንደ ባሕር የበዛ ውሃ ሰጣቸው፡፡
16ከዐለቱ ምንጭ አፈለቀ ውሃውም እንደ ወንዝ እንዲፈስ አደረገ
17እነርሱ ግን ኃጢአት ማድረጋቸውን ቀጠሉ፤ በምድረ በዳ በልዑል ላይ ዐመፁ፡፡
18የተመኙትን ምግብ በመጠየቅ፣ ሆን ብለው እግዚአብሔርን ተፈታተኑት፡፡
19እንዲህ በማለትም በእግዚአብሔር ላይ ተናገሩ፣ «ለመሆኑ፣ እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማዕድ ማዘጋጀት ይችላልን?»
20ዐለቱን ሲመታው ውሃ ተንዶለዶለ ጅረቶችም ጐረፉ፡፡ ታዲያ፣ እርሱ እንጀራንም መስጠት ይችላል? ለሕዝቡስ ሥጋ ማቅረብ ይችላል?
21ያህዌ ይህን ሲሰማ እጅግ ተቆጣ በያዕቆብ ላይ እሳት ነደደ በእስራኤልም ላይ ቁጣው ተቀጣጠሉ፡፡
22በእግዚአብሔር አላመኑም በእርሱም ማዳን አልተማመኑም፡፡
23ሆኖም እርሱ ከላይ ያሉትን ሰማያትን አዘዘ የሰማይንም በሮች ከፈተ
24ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ መና አዘነበላቸው የሰማይንም ምግብ ሰጣቸው፡፡
25ሰዎች የመላእክትን እንጀራ በሉ፡፡ ጠግበው እስከሚተርፍ ድረስ ምግብ ላከላቸው፡፡
26የምሥራቅን ነፋስ ከሰማይ አስነሣ የደቡብንም ነፍስ በኃይሉ አመጣ፡፡
27ሥጋን እንደ ዐፈር ብዙ ውፎችንም እንደ ባሕር አሸዋ አዘነበላቸው፡፡
28ሰፈራቸው መሓል በድንኳኖቻቸውም ዙሪያ አወረደ፡፡
29ስለዚህ እስኪጠግቡ ድረስ በሉ አጥብቀው የተመኙትን ሰጣቸው፡፡
30ነገር ግን ገና ምኞታቸውን ሳያረኩ፣ ምግቡ ገና አፋቸው ውስጥ እያለ፣
31የእግዚአብሔር ቁጣ እነርሱ ላይ ተነሣ የእስራኤልን ኃያላን ሰዎች ገደለ ምርጥ ወጣቶችንም በአጭር ቀጨ፡፡
32ይህም ሆኖ፣ ኃጢአት ማድረጋቸውን ቀጠሉ፤ ድንቅ ሥራዎቹንም አላመኑም፡፡
33ስለዚህ ዘመናቸውን አሳጠረ ዕድሜያቸውም በሽብር እንዲያልቅ አደረገ፡፡
34እርሱ በገደላቸው ጊዜ ፈለጉት ከልባቸው በመሻትም ወደ እርሱ ተመለሱ፡፡
35እግዚአብሔር ዐለታቸው፣ ልዑል አምላክ ታዳጊያቸው እንደ ሆነ አስቡ፡፡
36ነገር ግን በአፋቸው ሸነገሉት በአንደበታቸውም ዋሹት፡፡
37ልባቸው በእርሱ የጸና አልነበረም ለኪዳኑም ታማኞች አልነበሩም፡፡
38እርሱ ግን መሐሪ ስለሆነ ኃጢአታቸውን ይቅር አለ፤ እነርሱንም አላጠፋም ቁጣውን ብዙ ጊዜ ገታ መዐቱንም አላወረደም፡፡
39ካለፈ በኋላ እንደማይመለስ ነፋስ ሥጋ ለባሾች መሆናቸውን አሰበ፡፡
40በምድረ በዳ ስንት ጊዜ ዐመፁበት በበረሐስ ምን ያህል አሳዘኑት!
41ደግመው ደጋግመው እግዚአብሔርን ተፈታተኑት የእስራኤልንም ቅዱስ አስቆጡት፡፡
42ኃይሉን አላሰቡም፣ እነርሱን ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳነበትን፣ ቀንና ታላቁን ኃይሉን አላስታወሱም፡፡
43በግብፅ አገር፣ በዞዓር ሜዳ ያደረጋቸውን ታላላቅ ድንቆችና ምልክቶች ዘነጉ፡፡
44ከወንዞቻቸው ወሃ መጠጣት እንዳይችሉ የግብፃውያንን ወንዞች ወደ ደም ለወጠ፡፡
45ተናዳፊ የዝንብ ሰራዊት ሰደደባቸው፣ ጓጉንቸርም ላከባቸው፤ ምድራቸውንም አጠፋ፡፡
46ሰብላቸውን ለኩብኩባ፣ ምርታቸውንም ለአንበጣ ሰጠ፡፡
47የወይን ተክላቸውን በበረዶ የበለስ ዛፎቻቸውንም በውርጭ አጠፋ፡፡
48ከብቶቻቸውን በበረዶ በጐቻቸውንም በመብረቅ ገደለ፡፡
49ጽኑ ቁጣውን በላያቸው ሰደደ መዓቱን፣ የቅናቱንም ቁጣና መቅሠፍት ላከባቸው አጥፊ የመላእክት ሰራዊትም ሰደደባቸው፡፡
50ለቁጣው መንገድ አዘጋጀ፤ ከሞትም አላዳናቸውም፡፡ ነገር ግን ሕይወታቸውን ለመቅሠፍት አሳልፎ ሰጠ፡፡
51የዐፍላ ጉልበታቸው መጀመሪያ የሆኑትን በካም ድንኳኖች፣ በኩሮቻቸውንም ሁሉ በግብፅ ምድር ፈጀ፡፡
52ሕዝቡን ግን እንደ በግ አሰማራቸው በምድረ በዳ እንደ መንጋ መራቸው
53በሰላም ስለ መራቸው አልፈሩም ጠላቶቻቸውን ግን ባሕር ዋጣቸው፡፡
54ከዚያም ወደ ተቀደሰች ምድሩ፣ ቀኝ እጁም ወዳስገኘው ወደዚህ ተራራ አመጣቸው፡፡
55ሕዝቦችን ከፊታቸው አባረረ ምድራቸውንም ርስት አድርጐ አከፋፈላቸው፡፡ የእስራኤል ነገዶችን በጠላቶቻቸው ድንኳን አኖረ፡፡
56እነርሱ ግን አምላክን ተፈታተኑት በልዑልም ላይ ዐመፁ፤ ትእዛዞቹንም አልጠበቁም፡፡
57እንደ አባቶቻቸው ዐመፀኞችና ከዳተኞች ሆኑ፡፡ እንደማያስተማምን ጠማማ ቀስት ተወላገዱ፡፡
58በኮረብታ ማምለኪያዎቻቸው አስቆጡት በጣዖቶቻቸውም አስቀኑት፡፡
59እግዚአብሔር በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ እስራኤልንም ፈጽሞ ተወ፡፡
60በሰዎች መካከል የኖረባትን ድንኳን፣ በሴሎ የነበረች ማደሪያውን ተዋት፡፡
61የኃይሉን ምልክት አስማረካት፣ ክብሩንም ለጠላቶች እጅ አሳልፎ ሰጠ፡፡
62ሕዝቡን ለሰይፍ ዳረገ በርስቱም ላይ እጅግ ተቆጣ፡፡
63ጐልማሶቻቸውን እሳት በላቸው ለልጃገረዶቻቸውም የሰርግ ዘፈን አልተዘፈነላቸውም፡፡
64ካህናቶቻቸው በሰይፍ ተገደሉ መበለቶቻቸው ማልቀስ ተሳናቸው፡፡
65ጌታም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ የወይን ጠጅ ጠጥቶ ድፍረት እንደሚሰማው ጀግና ሆነ፡፡
66ጠላቶቹን መትቶ ወደ ኋላ መለሳቸው የዘላለም ውርደትንም አከናነባቸው፡፡
67የዮሴፍን ድንኳን ተዋት፣ የኤፍሬምንም ነገድ አልመረጠም፡፡
68ነገር ግን የይሁዳን ነገድና የወደዳትን የጽዮን ተራራ መረጠ፡፡
69መቅደሱን እንደ ሰማያት፣ እርሱ ለዘላለም እንደ መሠረታት ምድር ሠራት፡፡
70ባርያውን ዳዊትን መረጠ ከበጐች ጉረኖ ወሰደው፤
71ለሕዝቡ ለያዕቆብ፣ ለርስቱም ለእስራኤል እረኛ ሊደርገው የሚያጠቡ በጐችን ከመከተል አመጣው፡፡
72ዳዊትም በፍጹም ቅንነት ጠበቃቸው፤ በእጁ ብልኃትም መራቸው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።