1ድምፄን ከፍ አድርጌ ወደ እግዚአብሔር እጮኻለሁ ይሰማኝ ዘንድ ድምፄን ከፍ አድርጌ እግዚአብሔርን እጠራለሁ፡፡
2በመከራዬ ቀን ጌታን ፈለግሁት በሌሊትም ያለ ዕረፍት እጆቼን ዘረጋሁ፤ ነፍሴ አልጽናና አለች፡፡
3አምላኬ ሆይ፣ አንተን ባሰብሁ ቁጥር ቃተትሁ ባወጣሁ ባወረድሁ መጠን መንፈሴ ዛለች፡፡
4ዐይኖቼ እንዳይከደኑ አደረግህ መናገር እስኪሳነኝ ድረስ ታወክሁ፡፡
5የቀድሞውን ዘመን አሰብሁ የድሮውን ዘመን አወጠነጠንሁ፡፡
6በሌሊት ዝማሬዬን አስታወስሁ በጥልቅ በማሰብ እየሆነ ያለውን መረዳት ሞከርሁ፡፡
7እግዚአብሔር ለዘላለም ጥሎኛልን? ከእንግዲህስ ቸርነት አያደርግልኝምን?
8የኪዳን ታማኝነቱስ እስከ ወዲያኛው ተሻረን? የተስፋ ቃሉንስ ዘነጋ?
9እግዚአብሔር ቸርነቱን ረሳ? ወይስ ከቁጣው የተነሣ መራራቱን ትቶአልን? ሴላ
10እኔም፣ «የልዑል ቀኝ እጅ እንደ ተለወጠ ማሰቤ ይህ የእኔ ደካማነት ነው» አልሁ፡፡
11ያህዌ ሆይ፣ ሥራዎችህን ሁሉ አስታውሳለሁ ድሮ ያደረግኸውን ድንቅ ሥራ አስባለሁ፡፡
12ሥራዎችህን ሁሉ አሰላሰላለሁ ድንቅ ሥራህን ሁሉ አውጠነጥናለሁ፡፡
13አምላክ ሆይ፣ መንገድህ ቅዱስ ነው እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው?
14እግዚአብሔር ሆይ፣ አንተ ድንቆችን የምታደርግ አምላክ ነህ በሕዝቦች መካከል ኃይልህን ገለጥህ፡፡
15በታላቅ ኃይልህ ለሕዝብህ ለያዕቆብና ለዮሴፍ ልጆች ድል ሰጠሃቸው፡፡ ሴላ
16አምላክ ሆይ፣ ውሆች አዩህ ውሆች አንተን አይተው ፈሩ፤ ጥልቆችም ተነዋወጡ፡፡
17ደመኖች ውሃ አንጠባጠቡ፡፡ ሰማያት አንጐዳጐዱ ፍላጾችህም ዙሪያውን አንጸባረቁ፡፡
18የድምፅህ ነጐድጓድ ዐውሎ ነፋስ ውስጥ አስተጋባ የመብረቅ ብልጭታ ዓለምን አበራ ምድር ራደች ተንቀጠቀጠች፡፡
19መንገድህ በባሕር ውስጥ ነው መሄጃህም በታላቅ ውሃ ውስጥ ነው ዱካህንም ማንም አላየም፡፡
20በሙሴና በአሮን እጅ ሕዝብህን እንደ በግ መንጋ መራኸው፡፡