1አምላክ ሆይ፣ ለዘላለም የጣልኸን ለምንድነው? በመሰማሪያህ በጐችህስ ላይ ቁጣህ የነደደው ለምንድነው?
2ከጥንት ጀምሮ የመረጥኸውን ሕዝብ ርስትህ እንዲሆን የዋጀኸውን ነገድ፣ መኖርያህ ያደረግሃትን የጽዮን ተራራን አስብ፡፡
3ጠላት ለዘለቄታው ባድማ ያደረገውን መቅደስህ ውስጥ ያወደመውን ሁሉ ተመልከት፡፡
4ጠላቶችህ አንተ በመረጥኸው ቦታ መካከል ደነፉ፤ የጦርነት ዓርማቸውንም ምልክት አድርገው በዚያ አቆሙ፡፡
5እነርሱ ጥቅጥቅ ባለው ደን ውስጥ እንጨቶችን በመጥረቢያ የሚቆርጥ ሰው ይመስላሉ፡፡
6በእደ ጥበብ ያጌጠውን ሥራ ሁሉ፣ በመጥረቢያና በመዶሻ ሰባብረው አደቀቁት፡፡
7መቅደስህን አፍርሰው በእሳት አቃጠሉት የስምህን ማደሪ አረከሱ፡፡
8በልባቸውም፣ «ገና ሁሉንም እናጠፋቸዋለን!» አሉ፡፡ በምድሪቱ ያሉ የተቀደሱ ቦታዎችን ሁሉ አቃጠሉ፡፡
9የምናየው ምልክት የለም ከእንግዲህ ወዲህ ነቢያትም አይኖሩም፤ ይህ እስከ መቼ እንደሚቀጥል ከእኛ መካከል የሚያውቅ የለም
10አምላክ ሆይ፤ ጠላት የሚሳደበው እስከ መቼ ነው? ባላንጣስ ለዘላለም በስምህ ያላግጣልን?
11እጅህን፣ ቀኝ እጅህን የምትመልሰው ለምንድነው? ቀኝ እጅህን ከብብትህ አውጥተህ አጥፋቸው፡፡
12እግዚአብሔር ሆይ፣ ከጥንት ጀምሮ አንተ ንጉሤ ነህ ማዳንህንም በምድር ላይ አደረግህ፡፡
13በኃይልህ ባሕሩን ከፈልህ የባሕሩንም አውሬ ራስ ውሃ ውስጥ ቀጠቀጥህ፡፡
14የሌዋታንን ራሶች አደቀቅህ ሥጋውንም በምድረ በዳ ለሚኖሩ ምግብ አድርገህ ሰጠሃቸው፡፡
15ምንጮችንና ፈሳሾችን አፈለቅህ ወራጅ ወንዞችን አደረቅህ
16ቀኑ የአንተ ነው፣ ሌሊቱም የአንተ ነው፤ ፀሐይንና ጨረቃንም በቦታቸው አደረግህ፡፡
17የምድር ዳርቻዎችን ሁሉ የወሰንህ አንተ ነህ ክረምትና በጋ እንዲፈራረቁ አደረግህ፡፡
18ያህዌ ሆይ፣ ጠላቶችህ በአንተ ላይ መሳለቃቸውን ጅል ሰዎችም ስምህን መዳፈራቸውን ተመልከት፡፡
19የርግብህን ነፍስ ለዱር አራዊት አሳልፈህ አትስጥ፤ የተጨቆኑ ሕዝብህንም ለዘላለም አትርሳ፡፡
20የምድር ጨለማ ቦታዎች በዐመፅ ተሞልተዋልና ኪዳንህን አስብ፡፡
21የተጨቆኑት አፍረው አይመለሱ ችግረኞችና ጭቁኖች ስምህን ያመስግኑ፡፡
22አምላክ ሆይ፣ ተነሥ ለክብርህ ተሟገት ከንቱ ሰው ቀኑን ሙሉ አንተ ላይ ማላገጡን ተመልከት፡፡
23የባላጋራዎችህን ድንፋታ ዘወትር የሚሰነዝሩትን ስድብ አትርሳ፡፡