1ልባቸው ንጹሕ ለሆነ ለእስራኤል እግዚአብሔር ቸር ነው፡፡
2እኔ ግን እግሬ ሊሰናከል፣ አዳልጦኝም ልወድቅ ጥቂት ቀረኝ፡፡
3ክፉዎች ሲሳካላቸው ዐይቼ ቅናት አድሮብኝ ነበር፡፡
4እስኪሞቱ ድረስ ሕመም አያውቃቸውም ሰውነታቸውም ጤነኛና ጠንካራ ነው፡፡
5እንደ ሌሎች ሰዎች አይጨነቁም በሌሎች ላይ የሚደርሰው ስቃይ እነርሱ ላይ አይደርስም፡፡
6ትዕቢት የአንገት ጌጣቸው ነው ግፍን እንደ ልብስ ለብሰውታል፡፡
7የሰባ ዐይናቸውም ይጉረጠርጣል፣ ልባቸው ክፉ ሐሳብ ያፈልቃል፡፡
8በፌዝና በክፋት ይናገራሉ በእብሪት ተነሣሥተው ሌሎች ላይ ይዝታሉ፡፡
9አፋቸውን በሰማይ ያላቅቃሉ አንደበታቸውም ምድርን ያካልላል፡፡
10ስለዚህ ሕዝቡ ወደ እነርሱ ይመለሳል ውሃቸውንም በገፍ ይጠጣሉ፡፡
11«እግዚአብሔር እንዴት ሊያውቅ ይችላል በልዑልስ ዘንድ ዕውቀት አለ?» ይላሉ፡፡
12እንግዲህ ክፉዎች እንደዚህ ናቸው ሁልጊዜ እንደ ተዝናኑ ናቸው በሀብት ላይ ሀብት ይጨምራሉ፡፡
13ለካ ልቤን ንጹሕ ያደረግሁት እኔን በየዋህነት የታጠብሁት በከንቱ ኖሮአል!
14ቀኑን ሙሉ ተሰቃየሁ በየማለዳውም ተቀጣሁ፡፡
15እኔ እንደዚህ እናገራለሁ ብል ኖሮ የልጆችህን ትውልድ በከዳሁ ነበር፡፡
16እነዚህን ነገሮች ለመረዳት ብሞክርም በጣም ከባድ ሆነብኝ፡፡
17ወደ መቅደስህ እስክገባ ድረስ ምንም ማወቅ አልቻልሁም በኋላ ግን በክፉዎች ላይ ምን እንደሚደርስባቸው ተረዳሁ፡፡
18በእርግጥ በሚያዳልጥ ስፍራ አኑረሃቸዋል ወድቀው እንዲጠፉም አድርገሃል፡፡
19እንዴት ፈጥነው በቅጽበት ጠፉ! በከባድ ድንጋጤ ፈጽመው ወደሙ፡፡
20ሰው ከሕልሙ ሲነቃ እንደሚሆነው፣ ጌታ ሆይ፣ አንተም በምትነሣበት ጊዜ፣ እነርሱ በማለዳ እንደሚረሳ ሕልም ይሆናሉ፡፡
21ልቤ በጣም ተማረረች፣ እኔም እጅግ ቆሰልሁ፡፡
22ስሜት የሌለው አላዋቂ ሆንሁ በፊትህም እንደ እንስሳ ሆንሁ፡፡
23ይህም ሆኖ ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ አንተም ቀኝ እጄን ይዘኸኛል፡፡
24በምክርህ ትመራኛለህ በመጨረሻም በክብር ትቀበለኛለህ፡፡
25በሰማይ ከአንተ በቀር ማን አለኝ? በምድርም ከአንተ ሌላ የምፈልገው የለኝም፡፡
26ሥጋዬና ልቤ ደከሙ እግዚአብሔር ግን ለዘላለም የልቤ ብርታትና አለኝታ ነው፡፡
27እነሆ፣ ከአንተ የሚርቁ ይጠፋሉ ለአንተ ያልታመኑትንም ታጠፋቸዋለህ፡፡
28ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፣ ጌታ ያህዌን መጠጊያዬ አድርጌዋለሁ ሥራህንም ሁሉ እናገራለሁ፡፡