1እግዚአብአብሔር ሆይ፣ ለንጉሡ ትክክለኛ ፍርድን ለንጉሡም ልጅ ጽድቅህን ስጠው፡፡
2እርሱም ሕዝብህን በጽድቅ፣ ይዳኛል ለተቸገሩትም በትክክል ይፈርዳል፡፡
3ተራሮች ሰላምን፣ ኮረብቶችም የጽድቅን ፍሬ ያመጣሉ፡፡
4ለተቸገረው ሕዝብ ይሟገታል የችግረኞችን ልጆች ያድናል ጨቋኙንም ያደቀዋል፡፡
5ፀሐይ እስካለች ድረስ፣ ጨረቃም እስከምትኖርበት ከትውልድ እስከ ትውልድ ድረስ፣ አንተን ያከብራሉ፡፡
6በታጨደ መስክ ላይ እንደሚዘንብ ዝናብ ይውረድ እንደ ካፊያም ምድርን ያረስርስ፡፡
7በዘመኑ ጽድቅ ይስፈን ጨረቃም ብርሃንዋ በምትሰጥበት ዘመን ሁሉ ብርልጽግና ይብዛለት፡፡
8ግዛቱም ከባሕር እስከ ባሕር ከታላቁም ወንዝ እስከ ምድር ዳርቻ ይሁን፡፡
9በምድረ በዳ የሚኖሩ በፊቱ ይስገዱ ጠላቶቹም ወደ መሬት ወድቀው ትቢያ ይላሱ፡፡
10የተርሴስ ነገሥታትና ደሴቶች ስጦታ ያምጡለት የሳባና የዐረብ ነገሥታት እጅ መንሻ ያቅርቡለት፡፡
11ነገሥታት ሁሉ ይስገዱለት ሕዝቦችም ሁሉ ያገልግሉት፡፡
12ወደ እርሱ የሚጮኸውን ችግረኛ ሌላ ረዳት የሌለውን ድኻ ይረዳልና፡፡
13ለድኻና ለችግረኛ ይራራል ምስኪኖችንም ከሞት ያድናል፡፡
14ሕይወታቸውን ከጭቆናና ከግፍ ያድናል ደማቸውም በፊቱ የከበረ ነው፡፡
15ዕድሜው ይርዘም፤ ከዐረብ ወርቅ ይምጣለት፤ ዘወትር ይጸልዩለት የእግዚአብሔር በረከት አይለየው፡፡
16በምድሪቱ እህል ይትረፍረፍ በተራሮች አናት ያለው ሰብል ይወዛወዝ፡፡ ፍሬው እንደ ሊባኖስ ይንዠርገግ፤ በከተማ ያለውም ሕዝብ እንደ ሜዳ ሣር ይብዛ፡፡
17ስሙ ለዘላለም ጸንቶ ይኑር ዝናውም ፀሐይ በሚወጣበት ዘመን ሁሉ ይሰማ፤ ሕዝቦች በእርሱ ይባረኩ ሰዎች ሁሉ ቡሩክ ነህ ይበሉት፡፡
18ብቻውን ድንቅ የሚያደርግ የእስራኤል አምላክ ያህዌ ይባረክ፡፡
19ክቡር ስሙ ለዘላለም ይባረክ ምድር ሁሉ በክብሩ ትሞላ፡፡ አሜን፤ አሜን
20የእሴይ ልጅ የዳዊት ጸሎት እዚህ ላይ ተፈጸመ።