መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መጽሐፈ መዝሙር 71

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ያህዌ ሆይ፣ አንተን መጠጊያ አደረግሁ ፈጽሞ አልፈር፡፡
2በጽድቅህ ታደገኝ አስጥለኝም ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል አድነኝም፡፡
3በምሄድበት ቦታ ሁሉ አንተ መጠጊያ ዐምባ ሁነኝ፡፡ አንተ ዐለቴ፣ ምሽጌ ነህና እኔን ለማዳን ትእዛዝ ከአንተ ይውጣ፡፡
4አምላኬ ሆይ፣ ከዐመፀኛ ርኅራኄ ከሌለው ከጨካኝ እጅ ታደገኝ፡፡
5ጌታ ያህዌ ሆይ፣ አንተ ተስፋዬ ነህና ከልጅነቴ ጀምሮ በአንተ ታምኛለሁና፡፡
6ከተወለድሁ ጀምሮ በአንተ ተደገፍሁ ከእናቴ ማሕፀን ያወጣኸኝም አንተ ነህ ምስጋናዬ ዘወትር ለአንተ ነው፡፡
7አንተ ብርቱ መጠጊያየ ስለሆንህልኝ ሕይወቴ ለብዙዎች ምሳሌ ሆነ፡፡
8አፌ በምስጋናህ ተሞልቶአል ስለ ክብርህም ቀኑን ሙሉ እናገራለሁ፡፡
9በእርጅና ዘመኔ አትጣለኝ ጉልበቴም በደከመ ጊዜ አትተወኝ፡፡
10ጠላቶቼ ተነጋግረውብኛልና ሕይወቴን ማጥፋት የሚፈልጉም በእኔ በአንድነት አሢረዋል፡፡
11እነርሱም፣ «እግዚአብሔር ትቶታል፣ የሚያስጥለው የለምና ተከታትላችሁ ያዙት» አሉ፡፡
12አምላክ ሆይ፣ ከእኔ አትራቅ፣ አምላኬ ሆይ፣ እኔን ለማዳን ፍጠን፡፡
13ተቃዋሚዎቼ ይፈሩ፤ ይጥፉም ሊጐዱኝ የሚፈልጉ ይፈሩ ይዋረዱም፡፡
14እኔ ግን ዘወትር አንተን ተስፋ አደርጋለሁ በምስጋና ላይ ምስጋና አቀርብልሃለሁ፡፡
15ምንም እንኳ ማስተዋል ቢያዳግተኝ አንደበቴ ዘወትር ስለ ጽድቅህና ስለ ማዳንህ ይናገራል፡፡
16መጥቼ የጌታ ያህዌን ብርቱ ሥራ ዐውጃለሁ የአንተን ጽድቅ ብቻ እናገራለሁ፡፡
17እግዚአብሔር ሆይ፣ አንተ ከልጅነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ እኔም እስከ ዛሬ ድረስ ድንቅ ሥራህን እናገራለሁ፡፡
18አምላክ ሆይ፣ ሳረጅና ስሸብትም አትተወኝ እኔም ኃያልነትህን ለመጪው ትውልድ ብርታህንም ኃላ ለሚነሣ ሕዝብ እናገራለሁ፡፡
19አምላክ ሆይ፣ ጽድቅህ እስከ ሰማያት ከፍ ያለ ነው አንተ ታላላቅ ነገሮችን አድርገሃል አምላክ ሆይ፣ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?
20ብዙ ችግርና መከራ ብታሳየኝም ሕይወቴን እንደ ገና ታድሳለህ፡፡ ከምድር ጥልቅም እንደ ገና ታወጣኛለህ
21ክብሬን ትጨምራለህ ተመልሰህም ታጽናናኛለህ፡፡
22አምላኬ ሆይ፣ ስለ ታማኝነትህ በበገና አመሰግንሃለሁ፤ የእስራኤል ቅዱስ ሆይ፣ በመሰንቆ እዘምርልሃለሁ፡፡
23ለአንተ የምስጋና መዝሙር ሳቀርብ፣ ከንፈሮቼ በደስታ ይሞላሉ አንተ ያዳንሃት ነፍሴም እልል ትላለች፡፡
24አንደበቴ ቀኑን ሙሉ ስለ ጽድቅህ ያወራል፤ የእኔን መጐዳት የሚፈልጉ አፍረዋልና ተዋርደዋልምና፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።