1ያህዌ አምላኬ ሆይ፣ አንተ መጠጊያዬ ነህ! ከሚያሳድዱኝ ሁሉ አድነኝ ታደገኝም
2አለበለዚያ እንደ አንበሳ ይዘነጣጥሉኛል የሚያድነኝ በሌለበት ሁኔታ ያደቁኛል፡፡
3አምላኬ ያህዌ ሆይ፣ ጠላቶቼ አድርጓል የሚሉትን አላደረግሁም በእኔ ላይ ምንም በደል የለም፡፡
4በጐ ለዋለልኝ ክፉ አልመለስሁም፡፡ጠላቶቼን በከንቱ አልጐዳሁም፡፡
5የምናገረው እውነት ካልሆነ ጠላቴ አሳድዶ ይያዘኝ ሕይወቴን ከምድር ይቀላቅል ክብሬንም ከትቢያ ጋር ይደበልቅ፡፡ ሴላ
6ያህዌ ሆይ፣ በቁጣህ ተነሥ በጠላቶቼ ዛቻ ፍረድ አምላኬ ሆይ ንቃ ትእዛዝም አስተላልፍ፡፡
7ሕዝቦችን ሁሉ በዙሪያህ ሰብስብ ከላይም ሆነህ ግዛቸው፡፡
8ያህዌ በሕዝቦች ላይ ይፈርዳል ያህዌ ሆይ፣ እንደ ጽድቄ ፍረድልኝ ልዑል ሆይ፣ እንደ ንጽሕናዬ መልስልኝ፡፡
9ልብንና አእምሮን የምትመረምር ጻድቅ አምላክ ሆይ፣ የክፉዎችን ዐመፅ አጥፉ፤ ጻድቃንን ግን አጽና፡፡
10ጋሻዬ ልዑል እግዚአብሔር ነው፤ እርሱ ልበ ቅኖችን ያድናቸዋል፡፡
11እግዚአብሔር ጻድቅ ዳኛ ነው፤ ቁጣውንም በየዕለቱ የሚገልጥ አምላክ ነው፡፡
12ሰው በንስሐ የማይመለስ ከሆነ እግዚአብሔር ሰይፉን ይስላል፤ ለውጊያም ቀስቱን ይገትራል
13የሚገደሉ ጦር ዕቃዎቹን አዘጋጅቷል የሚንበለበሉትን ፍላጻዎቹንም አሰናድቶአል፡፡
14ክፋትን ያረገዘ፣ ክፉ ዕቅዶችን የፀነሰና አጥፊ ሐሰቶችን የወለደ ሰውን አስቡ፡፡
15ጥልቅ ጉድጓድ ይቆፍራል በቆፈረው ጉድጓድ እርሱ ይገባበታል፡፡
16ለሌሎች ያዘጋጀው ክፉ ዕቅድ ወደ ራሱ ይመለሳል፤ ዐመፃውም በገዛ ዐናቱ ላይ ይወርዳል፡፡
17ስለ ጽድቁ ያህዌን አመሰግናለሁ ለልዑል አምላክም እዘምራለሁ፡፡