1የውሃ ሙላት እስከ አንገቴ ደርሶአልና አምላክ ሆይ አድነኝ፡፡
2መቆሚያ ስላጣሁ በጥልቁ ረግረግ ውሃ ለመስጠም ተቃርቤአለሁ፡፡
3ብዙ ከመጮኼ የተነሣ ዛልሁ ጉሮሮየም ደረቀ፤ አምላኬን በመጠባበቅ ዐይኖቼ ፈዘዙ፡፡
4ያለ ምክንያት የሚጠሉኝ ከራስ ጠጉሬ ይልቅ በዝተዋል፤ ብዙ ጠላቶቼ እኔን ማጥፋት ይፈልጋሉ ያልሰረቅሁን ነገር መልሰህ አምጣ ተባልሁ፡፡
5እግዚአብሔር ሆይ አንተ ሞኝነቴን ታውቃለህ ኃጢአቴም ከአንተ የተሰወረ አይደለም፡፡
6የሰራዊት ጌታ ያህዌ ሆይ፣ አንተን ተስፋ የሚያደርጉ በእኔ ምክንያት አይፈሩ፡፡ የእስራኤል አምላክ ሆይ፣ አንተን አጥብቀው የሚሹህ በእኔ ምክንያት አይዋረዱ፡፡
7ስለ አንተ ስድብን ታግሼአለሁ እፍረትም ፊቴን ሸፍኖአል፡፡
8ለወንድሞቼ እንደ እንግዳ ለእናቴም ልጆች እንደ ባዕድ ሆንሁባቸው፡፡
9የቤትህ ቅናት በላችኝ ለአንተ የተሰነዘረው ስድብ እኔ ላይ ዐረፈ፡፡
10በምጾምበት ጊዜ በጣም አለቀስሁ እነርሱም ሰደቡኝ፡፡
11ማቅ በለበስሁ ጊዜ መተረቻ አደረጉኝ፡፡
12በከተማው ቅጥር ለሚቀመጡ የመነጋገሪያ ርእስ ለሰካራሞችም መዝፈኛ ሆንሁ፡፡
13ያህዌ ሆይ፣ እኔ ግን በወደድኸው ሰዓት ወደ አንተ እጸልያለሁ፡፡ በታላቅ ምሕረትህ፣ በማዳንህም ርግጠኝነት መልስልኝ፡፡
14ከረግረግ አውጣኝ እንድሰጥምም አትተወኝ፡፡ ከጥልቁ ውሃ ከእነዚያ ከሚጠሉኝም ታደገኝ፡፡
15ጐርፍ አያጥለቅልቀኝ ጥልቁ ውሃም አይዋጠኝ ጉድጓዱም ተደርምሶ አይዘጋብኝ፡፡
16ያህዌ ሆይ፣ የኪዳንህ ታማኝነት በጐ ናትና ስማኝ እንደ ምሕረትህም ብዛት መልስልኝ
17ከባርያህ ፊትህን አትሰውር ተጨንቄአለሁና ፈጥነህ መልስልኝ፡፡
18ወደ እኔ ቀርበህ አድነኝ ስለ ጠላቶቼም ተቤዠኝ፡፡
19የደረሰብኝን ስድብ፣ እፍረትና ውርደት ታውቃለህ ጠላቶቼንም አንድ በአንድ ታውቃቸዋለህ፡፡
20ስድብ ልቤን ሰብሮታልና ተስፋ ቆረጥሁ፡፡ የሚያዝንልኝ ፈለግሁ ማንም አልነበረም የሚያጽናናኝም ፈለግሁ ማንንም አላገኘሁም፡፡
21ምግቤን ከሐሞት ጋር ቀላቀሉ ለጥማቴም ሆምጣጤ ሰጡኝ፡፡
22በፊታቸው የቀረበው ማእድ ወጥመድ ይሁንባቸው ደኅና ነን ሲሉ አሽክላ ይሁንባቸው፡፡
23ማየት እንዳይችሉ ዐይናቸው ይጨልም ጀርባቸውም ዘወትር ይጉበጥ፡፡
24መዓትህን በላያቸው አፍስስ፤ የቁጣህም መቅሠፍት ድንገት ይድረስባቸው፡፡
25መኖሪያቸው ወና ይሁን! በድንኳኖቻቸውም የሚኖር አይገኝ፡፡
26አንተ የመታኸውን አሳደዋልና ያቆሰልሃቸውንም ሥቃይ አባብሰዋል፡፡
27በበደላቸው ላይ በደልን ጨምርባቸው ወደ ጽድቅህ ድል አይግቡ፡፡
28ከሕይወት መጽሐፍ ይደምሰሱ ከጻድቃንም ጋር አይጻፉ፡፡
29እኔ ግን ምስኪንና ሐዘነተኛ ነኝና አምላክ ሆይ፣ ማዳንህ ደግፎ ይያዘኝ፡፡
30የእግዚአብሔርን ስም በዝማሬ አመሰግናለሁ በውዳሴም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ፡፡
31ከበሬ ይልቅ፣ ቀንድና ጥፍር ካበቀለ እንቦሳ ይበልጥ ይህ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል፡፡
32ገሮች ይህን ባዩ ጊዜ ደስ ይላቸዋል እናንተ እግዚአብሔርን የምትሹ በርቱ፡፡
33ያህዌ ችግረኞችን ይሰማልና በእስራት ያለውንም ሕዝቡን አይንቅም፡፡
34ሰማይና ምድር፣ ባሕሮችና በውስጡ የሚንቀሳቀሱ ሁሉ ያመስግኑት፡፡
35እግዚአብሔር ጽዮንን ያድናታልና የይሁዳንም ከተሞች መልሶ ይሠራቸዋልና ሕዝቡም በዚያ ይሰፍራል ይወርሷታልም፡፡
36የባርያዎቹም ዘሮች ይወርሷታል ስሙንም የሚወዱ በዚያ ይኖራሉ፡፡