መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መጽሐፈ መዝሙር 65

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እግዚአብሔር ሆይ፣ በጽዮን ለአንተ ምስጋና ይገባል፤ ለአንተ የተሳልነውንም እንፈጽማለን፡፡
2ሥጋ ለባሽ ሁሉ ጸሎትን ወደምትሰማ ወደ አንተ ይመጣል፡፡
3ኃጢአት በርትቶብን በነበረ ጊዜ አንተ መተላለፋችንን ይቅር አልህ፡፡
4አንተ የመረጥኸው፣ በአደባባይህም እንዲኖር ወደ አንተ ያቀረብኸው ሰው ቡሩክ ነው፡፡ ከተቀደሰው መቅደስህ፣ ከቤትህም በረከት እንጠግባለን፡፡
5የምድር ዳርቻዎችና ከባሕሩ ማዶ ርቀው ያሉ ሁሉ ተስፋ አዳኛችን እግዚአብሔር ሆይ፣ በጽድቅህ ድንቅ አሠራር መልስልን፡፡
6በኃይልህ ተራሮችን አጽንተሃል ብርታትንም ታጥቀሃል፡፡
7አንተ የባሕሮችን ማስገምገም የማዕበላቸውንም ጩኸት የሕዝቦችንም ውካታ ጸጥ ታሰኛለህ፡፡
8ርቀው በምድር ዳርቻዎች ያሉ ካደረግኸው ድንቅ ሥራህ የተነሣ ይደነግጣሉ፡፡ ምሥራቅና ምዕራብ በደስታ እልል እንዲሉ ታደርጋቸዋለህ፡፡
9ዝናብ በማዝነብ ምድርን ትጐበኛለህ፤ ፍሬያማ በማድረግም ታበለጽጋታለህ፡፡ ለሰው ልጆች እህልን ይሰጡ ዘንድ የእግዚአብሔር ወንዞች ውሃን የተሞሉ ናቸው፡፡ አንተ እንዲህ እንዲሆን ወስነሃል፡፡
10ትልሟን ታረሰርሳለህ ወጣ ገባውን ታስተካክላለህ ዐፈሩን በካፊያ ታለሰልሳለህ ቡቃያዋንም ትባርካለህ፡፡
11ለዓመቱ በጐነትህን ታቀዳጀዋለህ፤ ሰረገላህም በረከትን ሞልቶ ይፈስሳል፡፡
12የምድረ በዳው ግጦሽ ቦታ እጅግ ለመለመ ኮረብቶችም ደስታን ለበሱ፡፡
13መሰማሪያዎች መንጋ በመንጋ ሆኑ ሸለቆዎች በሰብል ተሞሉ እልል እያሉም ዘመሩ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።