1እግዚአብሔር ሆይ፣ ከጠላቶቼ አድነኝ በእኔ ላይ ከሚነሡ ሰዎችም ጠብቀኝ፡፡
2ከክፉ አድራጊዎች ታደገኝ፣ ደም ከተጠሙ ሰዎችም አድነኝ፡፡
3ሕይወቴን ለማጥፋት አድብተዋልና ያህዌ ሆይ፣ ጨካኞች ያለ በደሌ፣ ያለ ኃጢአቴ በላዬ ተሰብስበው ዶለቱብኝ፡፡
4ምንም በደል ባይኖርብኝም ተዘጋጅተው መጡብኝ፤ አንተ ግን ሁኔታዬን ተመልከት እኔን ለመርዳትም ተነሥ፡፡
5የሰራዊት አምላክ የሆንህ ያህዌ አንተ የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕዝቦችን ለመቅጣት ተነሥ፣ ዐመፀኞችንም ያለ ምሕረት ቅጣቸው፡፡ ሴላ
6እንደ ውሻ እያላዘኑ በምሽት ተመልሰው ይመጣሉ በከተማዪቱም ይራወጣሉ፡፡
7ከአፋቸው የሚወጣውን ተመልከት ሰይፍ ከንፈራቸው ላይ አለ ደግሞም፣ «ማን ሊሰማን ይችላል?» ይላሉ፡፡
8አንተ ያህዌ ግን ትሥቅባቸዋለህ ሕዝቦችን ሁሉ በንቀት ታያቸዋለህ፡፡
9እግዚአብሔር ብርታቴ ሆይ አንተን እጠብቃለሁ፤ አምላኬ ሆይ አንተ መጠጊያዬ ነህና፡፡
10እግዚአብሔር በምሕረቱ ይገናኘኛል አምላኬ የጠላቶቼን ውድቀት ያሳየኛል፡፡
11እግዚአብሔር ጋሻችን ሆይ፣ ሕዝቤ እንዳይረሱ አትግደላቸው፤ በኃይልህ በትናቸው ዝቅ ዝቅም አድርጋቸው፡፡
12ከአፋቸው ስለሚወጣው ኃጢአት ከከንፈራቸውም ስለሚሰነዘረው ቃል በትዕቢታቸው ይያዙ፡፡ ከአፋቸው ስለ ወጣው መርገምና ውሸት
13በቁጣ አጥፋቸው፤ ፈጽመህም አስወግዳቸው፡፡ እግዚአብሔር በያዕቆብና በምድር ዳርቻ ሁሉ ገዢ መሆኑን ይወቁ፡፡
14እንደ ውሻ እያላዘኑ፣ በምሽት ተመልሰው ይመጣሉ፤ በከተማዪቱም ዙሪያ ይራወጣሉ፡፡
15ምግብ ፍለጋ ይራወጣሉ፤ ካልጠገቡም ያላዝናሉ፡፡
16እኔ ግን ስለ ኃይልህ እዘምራለሁ በማለዳም ስለ ዘላለማዊ ፍቅርህ እዘምራለሁ፡፡ አንተ መጠጊያዬ፣ በመከራዬም ቀን ዐምባዬ ነህና፡፡
17ብርታቴ ሆይ፣ በዝማሬ አመሰግንሃለሁ፤ እግዚአብሔር መጠጊያዬ የምትወደኝም አምላኬ ነህና፡፡