1ኃያሉ አምላክ ያህዌ ተናገረ ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያዋ ድረስ ምድርን ተናገረ፡፡
2ፍጹም ውብ ከሆነችው ከጽዮን እግዚአብሔር አበራ፡፡
3አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም የሚባላ እሳት በፊቱ ነው ኃይለኛ ዐውሎ ነፋስም በዙሪያው ነው፡፡
4ሕዝቡ ላይ ይፈርድ ዘንድ በላይ ያሉ ሰማያትንና ምድርን፣ «በመሥዋዕት ከእኔ ጋር ኪዳን የገቡትን
5ቅዱሳኔን ሁሉ ወደ እኔ ሰብስቡ» ብሎ ይጣራል፡፡
6ሰማያት ጽድቁን ያውጃሉ፡፡ እግዚአብሔርን ራሱ ፈራጅ ነው፡፡ ሴላ
7«ሕዝቤ ሆይ፣ ስማኝ ልንገርህ እስራኤል ሆይ፣ በአንተ ላይ ልመስክር፤ አምላክህ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፡፡
8ስለ መሥዋዕትህ አልነቅፍህም የሚቃጠል መሥዋዕትህ ሁልጊዜ በፊቴ ነው፡፡
9ከበረትህ ኮርማዎችን፣ ከጉሮኖህም አውራ ፍየሎችን አልወስድም
10የዱር አራዊት ሁሉ፣ በሺ ተራሮች ያለው እንስሳ ሁሉ የእኔ ነውና፡፡
11በየተራሮች ያሉ ወፎችን ሁሉ ዐውቃለሁ፡፡ በመስክ የሚገኙ እንስሶች ሁሉ የእኔ ናቸው፡፡
12ብራብ እንኳ ለአንተ አልናገርም ዓለምና በውስጧ ያለው ሁሉ የእኔ ነውና፡፡
13የኮርማዎችን ሥጋ እበላለሁን? ወይስ የፍየሎችን ደም እጠጣለሁን?
14የምስጋና መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርብ፤ ስእለትህንም ለልዑል አምላክ ክፈል፡፡
15በመከራ ቀን ጥራኝ እኔ እታደግሃለሁ፤ አንተም ታከብረኛለህ፡፡
16ዐመፀኛውን እግዚአብሔር እንዲህ ይለዋል ሕጌን ለማነብነብ፣ ኪዳኔንም በአፍህ ለመናገር ምን መብት አለህ?
17ትምህርቴን ጠልተሃል፤ ቃሌንም ወደ ኃላህ ጥለሃል፡፡
18ሌባውን ባየህ ጊዜ ከእርሱ ጋር ሮጥህ፣ ዕድል ፈንታህንም ከአመንዝሮች ጋር አደረግህ፡፡
19አፍህን ለክፋት፣ አንደበትህንም ሽንገላ ለመናገር አዋልህ፡፡
20ተቀምጠህ ወንድምህን አማኸው የእናትህንም ልጅ ስም አጠፋህ፡፡
21ይህን ሁሉ ስታደርግ ዝም አልሁህ ስለዚህ እኔም እንዳንተው የሆንሁ መሰለህ፡፡ አሁን ግን ፊት ለፊት ነገርህን ገልጩ እገሥጽሃለሁ፡፡
22እናንት እግዚአብሔርን የምትረሱ ይህን አስተውሉ፤ አለበለዚያ ብትንትናችሁን አወጣለሁ! የሚያስጥላችሁም የለም!
23የምስጋና መሥዋዕት የሚያቀርብልኝ ያከብረኛል፤ መንገዱን ቀና ለሚያደርግ የእግዚአብሔር ማዳን አሳየዋለሁ፡፡