1ልቤ መልካም ሐሳብ አፈለቀ ለንጉሡ የተቀኘሁትን ቅኔ አሰማለሁ አንደበቴ እንደ መልካም ጸሐፊ ብዕር ነው፡፡
2አንተ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ ውብ ነህ ከከንፈሮችህ ጸጋ ይፈስሳል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘላለም ባርኮሃል፡፡
3ኃያል ሆይ፣ ሰይፍህን በወገብህ ታጠቅ ግርማ ሞገስንም ተላበስ
4ስለ እውነት ስለ ፍትሕ ግርማን ተጐናጽፈህ ድል ለማድረግ ገሥግሥ ቀን እጅህ ድንቅ ነገር ታሳይ፡፡
5ፍላጻዎችን የሾሉ ናቸው ሕዝቦች ከእግርህ በታች ይወድቃሉ፡፡ ፍላጻዎችህ የንጉሡ ጠላቶችን ልብ ይወጋል፡፡
6አምላክ ሆይ፣ ዙፋንህ የዘላለም ዙፋን ነው በትረ መንግሥትህም የፍትሕ በትረ መንግሥት ነው፡፡
7ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃንም ጠላህ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከባልንጀሮችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ፡፡
8ልብስህ ሁሉ ከከርቤ፣ ከእሬትና ከብርጉድ በተቀመመ ሽቱ ያውዳል፤ በዝሆን ጥርስ ከተዋቡ ቤተ መንግሥቶች የሚወጣ የበገናና የመሰንቆ ድምፅ ደስ ያሰኝሃል፡፡
9በቤተ መንግሥትህ ከሚገኙ ወይዛዝርት መካከል፤ የነገሥታት ልጆች ይገኛሉ፤ ንግሥቲቱም በንጹሕ ወርቅ ያሸበረቀ ጌጤኛ ልብስ ተጐናጽፋ በቀኝህ በኩል ትቆማለች፡፡
10ልጄ ሆይ፣ አድምጪ አስተውይ፣ ጆሮሽንም አዘንብይ ሕዝብሽንና የአባትሽን ቤት እርሺ፡፡
11ንጉሥ በውበትሽ ተማርኮአል እርሱ ጌታሽ ነውና አክብሪው፡፡
12የጢሮስ ሴት ልጅ ስጦታ ይዛ ትመጣለች፤ ሀብታሞች ደጅ ይጠኑሻል፡፡
13በቤተ መንግሥት ያለችው ልዕልት አጊጣለች ልብሷም በወርቅ አሸብርቋል፡፡
14ጌጠኛ ልብሷን ለብሳ ወደ ንጉሡ ትገባለች፤ ደናግል ጓደኞቿም አጅበዋት ወደ አንተ ይመጣሉ፡፡
15በደስታና በሐሤትም አብረው ወደ ንጉሡ ቤት ይገባሉ፡፡
16ወንዶች ልጆችህ በአባቶችህ እግር ይተካሉ በምድር ሁሉ ላይ ገዦች አድርገህ ትሾማቸዋለህ፡፡
17ስምህን በትውልድ ሁሉ ዘንድ ለመታሰቢያ አደርጋለሁ ስለዚህ ሕዝቦች ከዘላለም እስከ ዘላለም ይወድሱሃል፡፡