መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መጽሐፈ መዝሙር 44

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1አምላክ ሆይ፣ በጆሮአችን ሰምተናል በቀድሞ ዘመን እነርሱ በነበሩበት ዘመን ያደረግኸውን አባቶቻችን ነግረውናል፡፡
2ሕዝቦችን በእጅህ አሳድዶህ አስወጣህ የእኛን ሕዝብ ግን ተከልህ ሕዝቦችን አደቀቅህ የእኛ ሕዝብ ግን በምድሩ እንዲኖር አደረግህ፡፡
3ምድሪቱን የወረሳት በሰይፋቸው አልነበረም፣ ያዳናቸውም የገዛ ክንዳቸው አልነበረም አንተ ወደድሃቸውና ቀኝ እጅህ፣ ክንድህና የፊትህ ብርሃን ይህን አደረገ፡፡
4እግዚአብሔር ሆይ፣ አንተ ንጉሤ ነህ ያዕቆብ ድል እንዲያገኝ የወሰንህ አንተ ነህ፡፡
5በአንተ ርዳታ ጠላቶቻችንን ድል እንነሣለን በስምህም ተቃዋሚዎቻችንን እንረግጣለን፡፡
6በቀስቴ አልተማመንምና ሰይፌም አያድነኝም፡፡
7አንተ ግን ከጠላቶቻችን አዳንኸን የሚጠሉንንም አሳፈርሃቸው፡፡
8ዘወትር በእግዚአብሔር እንመካለን ለዘላለምም ስምህን እንወድሳለን፡፡ ሴላ
9አሁን ግን ትተኸናል ለውርደትም ዳርገኸናል ከሰራዊታችንም ጋር አትወጣም፡፡
10ከጠላት ፊት እንድንሸሽ አደረግህ ባላንጣዎቻችንም ዘረፉን፡፡
11እንደሚታረዱ በጐች አደረግኸን በሕዝቦችም መካከል በተንኸን፡፡
12ሕዝብህን በርካሽ ዋጋ ሸጥኸው ከሽያጩም ያተረፍኸው የለም፡፡
13ለጐረቤቶቻችን ማፈሪያ በዙሪያችን ላሉትም መሣቂያና መዘባበቻ አደረግኸን፡፡
14በሕዝቦች ዘንድ ስድብ፣ በሰዎችም መካከል ራስ የሚነቀነቅብን አደረግኸን፡፡
15ውርደቴ ዘወትር በፊቴ ነው ፊቴም እፍረትን ተከናንቦአል፡፡
16ይህም ከዘላፊውና ከተሳዳቢው ድምፅ የተነሣ ከጠላትና ከተበቃይ የተነሣ ነው፡፡
17ይህ ሁሉ ቢደርስብንም፣ አንተን ግን አልረሳንም ለኪዳንህ ታማኝ መሆንንም አልተውንም፡፡
18ልባችን ከአንተ አልተመለሰም ርምጃችንም ከመንገድህ ወደ ኋላ አላለም፡፡
19አንተ ግን ተኩላዎች በሚውሉበት ቦታ ሰባብረህ ጣልኸን፤ በሞት ጥላም ሸፈንኸን፡፡
20የአምካችንን ስም ረስተን፣ እጆቻችንን ለባዕድ አማልክት ዘርግተን ቢሆን ኖሮ፣
21እግዚአብሔር ይህን ማወቅ ይሣነዋልን? እርሱ የሰውን ልብ ምስጢር የሚረዳ ነውና፡፡
22ያም ሆኖ፣ ቀኑን ሙሉ ስለ አንተ እንገደላለን እንደሚታረዱ በጐችም ተቆጠርን፡፡
23ጌታ ሆይ ንቃ፣ ለምንስ ትተኛለህ? ተነሥ፣ ለዘላለምም አትተወን፡፡
24ፊትህን ለምን ከእኛ ትሰውራለህ? መከራና ጭንቀታችን ለምን ችላ ትላለህ?
25እስከ ምድር ትቢያ ድረስ ወርደናል አካላችን ከምድር ጋር ተጣብቆአል፡፡
26እኛን ለመርዳት ተነሥ ስለ ኪዳን ታማኝነትህ ስትል ተቤዠን፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።