1ዋላ የምንጭ ውሃ እንደሚናፍቅ አምላኬ ሆይ፣ እኔም እግዚአብሔርን ተጠማሁ፡፡
2መቼ ደርሼ ነው የአምላክን ፊት የማየው?
3ጠላቶቼ ዘወትር፣ «አምላክህ የት አለ?» ስለሚሉኝ እንባዬ ቀንና ሌሊት ምግቤ ሆነ፡፡
4ነፍሴ በውስጤ እየፈሰሰች እነዚህን ነገሮች አስታውሳለሁ፣ ታላቅ ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር ቤት እየመራሁ በአእላፍ ሕዝብ መካከል በእልልታና በምስጋና መዝሙር እንዴት ከሕዝቡ ጋር እሄድ እንደ ነበር ትዝ አለኝ፡፡
5ነፍሴ ሆይ፣ ለምን ታዝኛለሽ? በውስጤስ ለምን ትታወኪያለሽ? የመድኃኒቴን አምላክ ዳግመኛ እንዳመሰግነው እግዚአብሔርን ተስፋሽ አድርጊ፡፡
6አምላኬ ሆይ፣ ነፍሴ በውስጤ አዝናለች ስለዚህ በዮርዳኖስ ምድር፣ ከአርሞንኤም ተራራ ጫፍ በሚዛር ተራራ አስብሃለሁ፡፡
7በፏፏቴህ ድምፅ ጥልቁ ጥልቁን ይጠራል ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በእኔ ላይ አለፈ፡፡
8ያም ሆኖ፣ ያህዌ ምሕረቱን በቀን ያዛል በሌሊትም ዝማሬው በእኔ ዘንድ አለ ይህም ለሕይወቴ አምላክ የማቀርበው ጸሎት ነው፡፡
9እግዚአብሔር ዐለቴን፣ «ለምን ረሳኸኝ? ጠላቴ ከደረሰብኝ ጭንቀት የተነሣ ለምን በሐዘን እመላለሳለሁ?» እለዋለሁ፡፡
10ጠላቶቼ ቀኑን ሙሉ፣ «አምክህ የት አለ?» እያሉ የሚያደርሱብን ፌዝ ዐጥንቶቼ ውስጥ እንደ ሰይፍ ሆነ፡፡
11ነፍሴ ሆይ፣ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ በውስጤ ትታወኪያለሽ? የመድኃኒቴን አምላክ ዳግመኛ እንዳመሰግነው እግዚአብሔርን ተስፋሽ አድርጊ፡፡