1በትዕግሥት ያህዌን ደጅ ጠናሁት እርሱም ዘንበል አለልኝ፤ ጩኸቴንም ሰማኝ፡፡
2ከአደገኛ ጉድጓድ፣ ከሚያዘቅጥም ጭቃ አወጣኝ፤ እግሮቼን፣ በዐለት ላይ አቆመ አካሄዴንም አጸና፡፡
3ለአምላካችን ምስጋና አዲስ መዝሙር በአፌ አኖረ፡፡ ብዙዎች ዐይተው ያከብሩታል፤ በያህዌም ይታመናሉ፡፡
4ያህዌን መታመኛው ያደረገ ወደ ትዕቢተኛው የማይመለከት የሐሰት አማልክት ወደሚከተሉት የሚያይ ቡሩክ ነው፡፡
5ያህዌ አምላኬ ሆይ፣ ያደረግኸው ድንቅ ነገር ብዙ ነው ለእኛ ያለህም ሐሳብ ከቁጥር በላይ ነው፤ ላወራው ልናገረው ብል ስፍር ቁጥር አይኖረውም፡፡
6መሥዋዕትንና መባን አልፈለግህም ጆሮዎቼን ግን ከፈትህ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትንና የኃጢአት መሥዋዕትን አልጠየቅህም፡፡
7እኔም እንዲህ አልሁ፣ «እነሆ፣ መጥቻለሁ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ ተጽፎአል፤
8አምላኬ ሆይ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ ሕግህም ልቤ ውስጥ ነው፡፡
9በታላቅ ጉባኤ ውስጥ ጽድቅህን ዐወጅሁ ያህዌ ሆይ፣ ይህን ከማድረግ ወደ ኋላ አለማለቴንም አንተ ታውቃለህ፡፡
10ጽድቅህን በልቤ ውስጥ አልሸሸግሁም፤ ታማኝነትህንና ማዳንህን ተናገርሁ ምሕረትህንና እውነትህን ከታላቅ ጉባኤ አልደበቅሁም፡፡
11ያህዌ ሆይ ምሕረትህን አትንፈገኝ ቸርነትህና ታማኝነትህ ዘወትር ይጠብቁኝ፡፡
12ስፍር ቁጥር የሌለው ችግር ከብቦኛል የኃጢአቴ ብዛት ስለ ያዘኝ ማየት ተስኖኛል፤ ከራሴ ጠጉር ይልቅ በዝቶአል፤ ልቤም ከድቶኛል፡፡
13ያህዌ ሆይ፣ እኔን ለማዳን ፈቃድህ ይሁን እኔን ለመርዳትም ፍጠን፡፡
14ነፍሴን ለመንጠቅ የሚፈልጉ ይፈሩ፤ ይዋረዱም፡፡ ጉዳቴን የሚሹ ተዋርደው በመጡበት ይመለሱ፡፡
15በእኔ ላይ፣ «እሰይ! እሰይ!» የሚሉ በራሳቸው እፍረት ይደንግጡ
16አንተን የሚፈልጉ ሁሉ ደስ ይበላቸው ሐሤትም ያድርጉ፤ ማዳንህን የሚወዱ ዘወትር፣ «ያህዌ ከፍ ከፍ ይበል» ይበሉ፡፡
17እኔ ችግረኛና ምስኪን ነኝ ጌታ ግን ያስብልኛል፡፡ አንተ ረዳቴ ነህ እኔን ለማዳን ፍጠን አምላኬ ሆይ አትዘግይ፡፡