1በክፉዎች ምክንያት አትበሳጭ ኃጢአት በሚሠሩም አትቅና፤
2እንደ ሣር ቶሎ ይደርቃሉና እንደ ለመለመ ቅጠልም ይጠወልጋሉ፡፡
3በያህዌ ተማመን፤ መልካምንም አድርግ በምድሪቱ ተቀመጥ፤ ታምነህም ተሰማራ፡፡
4በያህዌ ደስ ይበልህ የልብህንም ፍላጐት ይሰጥሃል፡፡
5መንገድህን ለያህዌ አደራ ስጥ በእርሱ ታመን እርሱም ያከናውንልሃል፡፡
6ጽድቅህን እንደ ብርሃን ያንተንም ንጽሕና እንደ ቀትር ፀሐይ ያበራዋል፡፡
7በያህዌ ፊት ጸጥ በል፤ በትዕግሥትም ተጠባበቀው፡፡ ነገር በተሳካለት፣ ክፋትንም በሚሸርብ ሰው አትቅና
8አትቆጣ፤ ተስፋም አትቁረጥ መከራን ከማብዛቱ ውጪ ምንም ስለማይጠቅምህ አትከፋ፡፡
9ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉ ያህዌን የሚጠባበቁ ግን ምድሪቱን ይወርሳሉ፡፡
10ብዙም ሳይቆይ ክፉ ሰው ይጠፋል ብትፈልግም ቦታውን አታገኘውም፡፡
11ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ በታላቅ ሰላምም ደስ ይላቸዋል፡፡
12ክፉዎች ጻድቃን ላይ ያሤራሉ ጥርሳቸውንም ያፋጩባቸዋል፡፡
13መጥፊያ ቀናቸው እንደ ደረሰ ስለሚያውቅ ጌታ ይስቅባቸዋል፡፡
14ድኾችንና ችግረኞችን ለመጣል ልበ ቅኖችንም ለመግደል ክፉዎች ሰይፋቸውን መዘዙ፤ ቀስታቸውንም ገተሩ፡፡
15ሰይፋቸው የገዛ ልባቸውን ይወጋል ቀስታቸውም ይሰበራል፡፡
16ከክፉ ሰው ብዙ ሀብት ይልቅ፣ የጻድቅ ጥቂት ሀብት ይበልጣል፡፡
17የክፉዎች ክንድ ይሰበራልና ያህዌ ግን ጻድቃንን ይደግፋቸዋል፡፡
18ያህዌ ያለ ነቀፋ የሚመላለሱትን ዕለት ዕለት ይጠብቃቸዋል፡፡ ርስታቸውም ለዘላለም ይኖራል፡፡
19በክፉ ቀን አያፍሩም በራብ ዘመንም የሚበሉትን አያጡም፡፡
20ክፉዎች ግን ይጠፋሉ የያህዌ ጠላቶች እንደ መስክ ውበት ይሆናሉ፡፡ እንደ ጢስም በንነው ይጠፋሉ፡፡
21ኃጢአተኛ ይበደራል፣ ግን መልሶ አይከፍልም ጻድቅ ግን በልግስና ይሰጣል፡፡
22እግዚአብሔር የባረካቸው ምድርን ይወርሳሉ እርሱ የረገማቸው ግን ይጠፋሉ፡፡
23የሰውን አካሄድ የሚያጸና ያህዌ ነው በመንገዱም ደስ ይለዋል፡፡
24ያህዌ በእጁ ደግፎ ስለሚይዘው ቢሰናከል እንኳ አይወድቅም፡፡
25ጐልማሳ ነበርሁ፤ አሁን አርጅቻለሁ ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እንጀራ ስለምን አላየሁም፡፡
26ጻድቅ ሁልጊዜ በልግሥና ይሰጣል፣ ደግሞም ያበድራል ልጆቹም የተባረኩ ይሆናሉ፡፡
27ከክፉ ራቅ መልሙንም አድርግ ለዘላለምም በሰላም ትኖራለህ፡፡
28ያህዌ ፍትሕ ይወዳልና ታማኞቹንም በፍጹም አይጥልም፤ ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል፡፡ የኃጢአተኛው ዘር ግን ይጠፋል፡፡
29ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ፡፡
30የጻድቅ አፍ ጥበብን ይናገራል አንደበቱም ፍትሕን ያወራል፡፡
31የአምላኩ ሕግ ልቡ ውስጥ ነው አካሄዱም አይሰናከልም፡፡
32ኃጢአተኛው ጻድቅን ይመለከተዋል ሊገድለውም ይፈልጋል፡፡
33እግዚአብሔር ግን በእጁ አይጥለውም ፍርድ ፊት ሲቀርቡም አይረታም፡፡
34ያህዌን ደጅ ጥና፤ መንገዱንም ጠብቅ እርሱም ምድርን እንድትወርስ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፡፡ ክፉዎች ሲጠፋ ታያለህ፡፡
35ክፉና ጨካኙን ሰው ምቹ መሬት ላይ እንዳለ ዛፍ ለምልሞ አየሁት
36ተመልሼ ስመጣ ግን በቦታው አልበረም፤ ፈለግሁ ላገኘው ግን አልቻልሁም፡፡
37ጻድቅን ሰው ተመልከት ቅን የሆነውንም ሰው እይ የሰላም ሰው ተስፋ አለውና፡፡
38ኃጠአተኞች ግን ፈጽሞ ይደመስሳሉ ዘራቸውም ይወገዳል፡፡
39የጻድቃን ድነት ከያህዌ ዘንድ ነው በመከራም ጊዜ ይጠብቃቸዋል፡፡
40ያህዌ ይረዳቸዋል፤ ደግሞም ይታደጋቸዋል፡፡ ከክፉዎች እጅ ነጥቆ ያወጣቸዋል እርሱን መጠጊያ አድርገዋልና ያድናቸዋል፡፡