1ያህዌ ሆይ፣ የሚቃወሙኝን ተቃወማቸው፤ የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው፡፡
2ትልቁንና ትንሹን ጋሻ ያዝ እኔንም ለመርዳት ተነሥ፡፡
3በሚያሳድዱኝ ላይ ጦርና ሰይፍህን ምዘዝና ነፍሴን «እኔ አዳኝሽ ነኝ» በላት፡፡
4ሕይወቴን የሚፈልጓት ይፈሩ ይዋረዱም እኔን ለመጉዳት የሚያደቡ አፍረው ወደ ኋላቸው ይመለሱ፤ ግራ ይጋቡ፡፡
5በነፋስ ፊት እንዳለ እብቅ ይሁኑ የያህዌም መልአክ ያሳድዳቸው፡፡
6መንገዳቸው ጨለማና ድጥ ይሁን የያህዌ መልአክ ያባርራቸው፡፡
7ያለ ምክንያት ወጥመድ ዘርግተውብኛል ያለ ምክንያት ሕይወቴን ለማጥፋት ጉድጓድ ቆፍረዋል፡፡
8ጥፋት በድንገት ይምጣባቸው የዘረጉት ወጥመድ ይያዛቸው ጉድጓድ ውስጥ ወድቀው ይጥፉ፡፡
9እኔ ግን በያህዌ ደስ ይለኛል በማዳኑም ሐሤት አደርጋለሁ፡፡
10ዐጥንቶቼ ሁሉ፣ «ያህዌ ሆይ፣ ድኻውን ከእርሱ ከሚበረቱ፣ ችግረናውንና ምስኪኑን ከቀማኞች እጅ የሚያድን እንደ አንተ ያለ ማን ነው?» እለዋለሁ፡፡
11ሐሰተኛ ምስክሮች ተነሥተውብኛል በሐሰትም ይከስሱኛል፡፡
12እኔን ብቸኛ አድርገው በመልካም ፈንታ ክፉ መለሱልኝ፡፡
13እኔ ግን እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፤ ለእነርሱ ጾምሁ፤ አንገቴን ደፋሁ፡፡
14ለወንድሙ እንደሚያለቅስ ሰው አዘንሁ ለእናቱ ልጅ እንደሚያዝን ሰው ሆንሁ፡፡
15እኔ በተሰናከልሁ ጊዜ ደስ ብሎአቸው ተሰበሰቡ ግፈኞች በድንገት ተሰበሰቡብኝ ያለ ዕረፍትም ቦጫጨቁኝ፡፡
16እንደ ምናምንቴዎች አፌዙብኝ ጥርሳቸውንም አፋጩብኝ፡፡
17ጌታ ሆይ፣ እስከ መቼ ዝም ብለህ ታያለህ? ነፍሴን በእነርሱ ከመጠቃት ሕይወቴንም ከአንበሶች አድናት፡፡
18በታላቅ ጉባኤ መካከል አመሰግንሃለሁ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበትም እወድስሃለሁ፡፡
19ያለ ምክንያት የሚጠሉኝ ጠላቶቼ በእኔ ላይ ደስ እንዲላቸው፣ ተንኰላቸውንም እንዲፈጽሙብኝ አታድርግ፡፡
20የሰላም ቃል ከአፋቸው አይወጣም ነገር ግን በምድሪቱ በጸጥታ በሚኖሩት ላይ ተንኮል ይሸርባሉ፡፡
21አፋቸውን አስፍተው በመክፈት፣ «እሰይ! እሰይ! በዐይናችን አየነው» አሉ፡፡
22ያህዌ ሆይ፣ ይህን አይተሃልና ዝም አትበል ጌታ ሆይ፣ ለእኔም አትራቅ፡፡
23አምላኬ ጌታዬ፣ ለእኔ ለመሟገት ተነሥ ልትከራከርልኝም ተንቀሳቀስ፤
24ያህዌ ሆይ፣ በጽድቅህ ፍረድልኝ በእኔም ላይ ደስ አይበላቸው፡፡
25በልባቸው፣ «እሰይ፣ ያሰብነው ተሳካ» አይበሉ፤ «ዋጥ አደረግነውም» አይበሉ፡፡
26በጭንቀቴ ደስ የሚላቸው ይፈሩ፤ ግራም ይጋቡ፡፡ በእኔ ላይ የሚያፌዙ፤ እፍረትና ውርደት ይልበሱ፡፡
27ፍትሕ ማግኘቴን የሚፈልጉ እልል ይበሉ ሐሤትም ያድርጉ፣ ዘወትርም፣ «የባርያው ሰላም ደስ የሚለው ያህዌ ይመስገን» ይበሉ፡፡
28ያኔ የአንተን ጽድቅ እናገራለሁ ቀኑን ሙሉ አመሰግንሃለሁ፡፡