1መተላለፉ ይቅር የተባለለት ኃጢአቱም የተሸፈነለት ሰው ቡሩክ ነው፡፡
2ያህዌ በደሉን የማይቆጥርበት በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው ቡሩክ ነው፡፡
3ቀኑን ሙሉ በመቃተቴ ዝም ባልሁ ጊዜ፣ አጥንቶቼ ተበላሹ፡፡
4ቀኑን ሙሉ እጅህ ከብዳኛለች ብርታቴም የበጋ ትኩሳት እንደ መታው ነገር ከውስጤ ተሟጠጠ፡፡ ሴላ
5በዚያን ጊዜ ኃጢአቴን ለአንተ ተናዘዝሁ በደሌንም ከአንተ አልሰወርሁም ደግሞም፣ «መተላለፌን ለያህዌ እናዘዛለሁ» አልሁ አንተም የኃጢአቴን በደል ይቅር አልህ፡፡ ሴላ
6ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው በጭንቅ ጊዜ ወደ አንተ ይጸልይ ብርቱ ጐርፍ ሞልቶ ቢያጥለቀቅ እንኳ፣ ወደ እነዚህ ሰዎች አይቀርብም፡፡
7አንተ መሸሸጊያዬ ነህ፤ ከመከራም ታወጣኛለህ፡፡ በድል ዝማሬ ትከበኛለህ፡፡ ሴላ
8አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበት መንገድ እመራሃለሁ እመክርሃለሁ ዐይኔንም አንተ ላይ አደርጋለሁ፡፡
9ወደምትፈልጉት ቦታ እንዲሄዱላችሁ በልጓምና በልባብ እንደሚገሩት ማስተዋል እንደሌለው ፈረስና በቅሎ አትሁኑ፡፡
10የክፉዎች ሐዘን ይበዛል በያህዌ የሚታመነውን ግን የእርሱ ኪዳን ታማኝነት ይከብበዋል፡፡
11ጻድቃን ሆይ፣ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ ልበ ቅኖች ሆይ፣ እልል በሉ፡፡