1ያህዌ ሆይ፣ አንተን ተማጽኛለሁና እፍረት ከቶ አይድረስብኝ፤ በጽድቅህም ታደገኝ፡፡
2ጌታ ሆይ፣ አድምጠኝ ፈጥነህም ታደገኝ የመማጸኛ ዐለት፣ የመዳኛም ምሽግ ሁነኝ፡፡
3አንተ ዐለቴና ዐምባዬ ነህ ስለ ስምህ ስትል ምራኝ መንገዱንም አሳየኝ፡፡
4አንተ መታመኛዬ ነህና በስውር ከተዘረጋብኝ ወጥመድ አውጣኝ፡፡
5መንፈሴን በእጅህ ዐደራ እሰጣለሁ የእውነት አምላክ ያህዌ ሆይ፣ ተቤዠኝ፡፡
6ከንቱ ጣዖታትን የሚያገለግሉትን ጠላሁ እኔ ግን በያህዌ እታመናለሁ፡፡
7መከራዬን አይተሃልና የነፍሴን ጭንቀት ዐውቀሃልና እኔ በኪዳን ታማኝነትህ ደስ ይለኛል፤ ሐሤትም አድርጋለሁ፡፡
8በጠላቴ እጅ አሳልፈህ አልሰጠኸኝም እግሮቼን ሰፊ ቦታ ላይ አቆምሃቸው፡፡
9ያህዌ ሆይ፣ ጭንቀት ውስጥ ነኝና ማረኝ ዐይኖቼ በሐዘን ደክመዋል፤ ነፍስና ሥጋዬም ዝለዋል፡፡
10ሕይወቴ በጭንቀት ዕድሜዬም በመቃተት አለቀ፡፡ ከኃጢአቴ የተነሣ ጉልበቴ ከዳኝ ዐጥንቴም ደቀቀ፡፡
11ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ ለጐረቤቶቼ መዘባበቻ ለሚያውቁኝ ሰዎች መሳለቂያ ሆኛለሁ መንገድ ላይ የሚያገኙኝም ይሸሹኛል፡፡
12ማንም እንደማያስበው እንደ ሞተ ሰው ተረሳሁ እንደ ተሰበረ የሸክላ ዕቃም ተቆጠርሁ፡፡
13የብዙዎችን ሹክሹክታ ሰምቻለሁ በዙሪያዬም የሽብር ወሬ አለ በእኔ ላይ ባሤሩ ጊዜ ሕይወቴን ለማጥፋት ዶለቱ፡፡
14እኔ ግን ያህዌ ሆይ፣ በአንተ እተማመናለሁ «አንተ አምላኬ ነህ» አልሁ፡፡
15ዘመኔ ሁሉ በእጅህ ነው፡፡ ከጠላቶቼና ከሚያሳድዱኝ ሰዎች እጅ አድነኝ፡፡
16ፊትህን ባርያህ ላይ አብራ፡ በኪዳን ታማኝነትህ አድነኝ፡፡
17ያህዌ ሆይ፣ አንተን ጠርቻለሁና ለእፍረትና ለውርደት አትዳርገኝ፡፡ ክፉዎች ግን ይፈሩ፤ ይዋረዱ ሲኦል ገብተው ጸጥ ይበሉ፡፡
18ጻድቁ ላይ በእብሪት የሚናገሩ ትዕቢትና ንቀትን የተሞሉ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ፡፡
19ለሚፈሩህ የሰወርኸው፣ በአንተም ለሚታመኑ በሰው ልጆች ሁሉ ፊት የምታደርገው እንዴት ታላቅ ነው!
20ከሰዎች ሤራ በማደሪያህ ውስጥ ትሸሽጋቸዋለህ፡፡
21በተከበበች ከተማ ለእኔ ድንቅ ታማኝነቱን የገለጠ ያህዌ ይባረክ፡፡
22እኔ ግን ባለ ማስተዋል፣ «ከእንግዲህ ከዐይንህ ፊት ተወግጃለሁ» ብዬ ነበር፤ ሆኖም፣ አንተ እንድትረዳኝ ስጮኽ ሰማኸኝ፡፡
23እናንተ ታማኝ ተከታዮቹ ሁሉ ያህዌን ወደዱት ያህዌ ታማኞችን ይጠብቃል ለእብሪተኞች ግን የእጃቸውን ይሰጣቸዋል፡፡
24እግዚአብሔርን ተስፋ የምታደርጉ ሁሉ በርቱ ልባችሁም ይጽና፡፡