1ያህዌ ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው የሚያስፈራኝ ማን ነው? ያህዌ የሕይወቴ መታመኛዋ ነው የሚያስደነግጠኝ ማን ነው?
2ክፉ አድራጊዎች ሥጋዬን ለመብላት በቀረቡኝ ጊዜ፣ ባላጋራዎቼና ጠላቶቼ ተሰነካክለው ወደቁ፡፡
3ሰራዊት ቢከብበኝ እንኳ፣ ልቤ አይፈራም ጦርነት ቢነሣብኝ እንኳ ልበ ሙሉ ነኝ፡፡
4ያህዌን አንዲት ነገር ለመንሁት፣ እርሷንም እሻለሁ፤ ያም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በያህዌ ቤት እንድኖር፣ የመቅደሱን ውበት እንዳይና መቅደሱ ውስጥ አሰላስል ዘንድ ነው፡፡
5በመከራዬ ቀን በድንኳኑ ይሰውረኛናል በዐለትም ላይ ያቆመኛል፡፡
6ያኔ በዙሪያዬ ባሉ ጠላቶቼ ላይ ራሴ ከፍ ከፍ ይላል በድንኳኑም የደስታ መሥዋዕት እሠዋለሁ ለያህዌ እቀኛለሁ፤ እዘምርለታለሁም፡፡
7ያህዌ ሆይ፣ ወደ አንተ ስጮኽ ድምፄን ስማ ማረኝ መልስልኝም፡፡
8«ፊቴን ፈልጉ» ባልህ ጊዜ ልቤ፣ «የያህዌን ፊት እፈልጋለሁ» አለች፡፡
9ፊትህን ከእኔ አትሰውር ተቆጥተህም ባርያህን ገሸሽ አታድርገው! መቼም አንተ ረዳቴ ነህና የመድኃኒቴ አምላክ ሆይ፣ አትተወኝ፣ አትጣለኝም
10አባትና እናቴ ቢተውኝ እንኳ ያህዌ ይቀበለኛል፡፡
11ያህዌ ሆይ መንገድህን አስተምረኝ ስለ ጠላቶቼም በቀናች መንገድ ምራኝ፡፡
12ሐሰተኛ ምስክሮች ተነሥተውብኛልና ጠላቶቼ እንደ ፈለጉ እንዲያደርጉብኝ አትተወኝ፡፡ እነርሱ ዐመፃን ይረጫሉ!
13በሕያዋን ምድር የያህዌን መልካምነት እንደማይ ባላምን ኖሮ ምን እሆን ነበር?
14እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ አይዞህ በርታ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ