1ያህዌ ሆይ፣ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁ!
2አምላኬ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ፡፡ እባክህ አታሳፍረኝ፤ አታዋርደኝ ጠላቶቼም በእኔ ላይ ደስ እንዲላቸው አታድርግ፡፡
3አንተን ተስፋ የሚያደርጉ ከቶ አያፍሩም፤ እንዲያው ያለ ምክንያት የሚያታልሉ ግን ያፍራሉ፡፡
4ያህዌ ሆይ፣ አካሄድህን አሳውቀኝ መንገድህንም አስተምረኝ፡፡
5በእውነትህ ምራኝ አስተምረኝም፤ አንተ የድነቴ አምላክ ነህና ቀኑን ሙሉ በአንተ ታመንሁ፡፡
6ያህዌ ሆይ፣ ከጥንት ጀምሮ የነበሩ ምሕረትህንና ፍቅርህን አስብ፡፡
7የልጅነቴን ኃጢአት፣ መተላለፌንም አታስብብኝ፤ ያህዌ ሆይ፣ እንደ ቸርነትህ ብዛት እንደ ምሕረትህም መጠን አስበኝ፡፡
8ያህዌ መልካም ቅን ነው፤ ስለዚህ ኃጢአተኞችን መንገድን ያስተምራቸዋል፡፡
9ትሑታንን በትክክለኛው መንገድ ይመራቸዋል መንገዱንም ያስተምራቸዋል
10ኪዳኑንና ሥርዐቱን ለሚጠብቁ የያህዌ መንገድ ሁሉ ቸርነትና እውነት ነው፡፡
11ያህዌ ሆይ፣ ኃጢአቴ እጅግ ብዙ ነውና ስለ ስምህ ይቅር በለኝ
12ያህዌን የሚፈራ ሰው ማን ነው ጌታ በመረጠው መንገድ ያስተምረዋል፡፡
13ዘመኑን በተድላ ደስታ ያሳልፋል ዘሮቹም ምድርን ይወርሳሉ፡፡
14ያህዌ ለሚታዘዙት ሁሉ ወዳጃቸው ነው ለእነርሱ የገባውንም ኪዳን ያጸናል፡፡
15ዐይኖቼ ዘወትር ወደ ያህዌ ናቸው እግሮቼን ከወጥመድ የሚያላቅቃቸው እርሱ ነው፡፡
16እኔ ብቸኛና ምስኪን ነኝና ወደ እኔ ተመለስ ማረኝም፡፡
17የልቤ ሐዘን በዝቶአል ከጭንቀቴ አወጣኝ፡፡
18መከራዬንና ጭንቀቴን ተመልከት ኃጢአቴን ሁሉ ይቅር በል፡፡
19ጠላቶቼ እንዴት እንደ በዙ እይ፤ እንዴት አምርረው እንደሚጠሉኝ ተመልከት፡፡
20ነፍሴን ጠብቃት፤ ታደገኝም በአንተ ተማምኛለሁና አልዋረድ፤ አልፈር፡፡
21አንተን ተስፋ አድርጌአለሁና ታማኝነትና ቅንነት ይጠብቁኝ
22ያህዌ ሆይ፣ እስራኤልን ከመከራው ሁሉ አድነው፡፡