መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መጽሐፈ መዝሙር 22

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ? እኔን ለማዳን፣ ከመቃተቴም ቃል ለምን ራቅህ?
2አምላኬ ሆይ፣ በቀን ወደ አንተ እጮኻለሁ፣ አንተ ግን አልመለሰህልኝም በሌሊት እንኳ አላረፍሁም፡፡
3አንተ ቅዱስ ነህ በእስራኤል ምስጋና ውስጥ እንደ ንጉሥ ትቀመጣለህ፡፡
4አባቶቻችን በአንተ ተማመኑ፣ በአንተ ተማመኑ አንተም ታደግሃቸው፡፡
5ወደ አንተ ጮኹ፤ እነርሱም ዳኑ በአንተ ተማመኑ፤ እነርሱም አላፈሩም፡፡
6እኔ ግን ትል እንጂ፣ ሰው አይደለሁም ለሰዎች ማላገጫ፣ በሕዝብም ዘንድ የተናቅሁ ነኝ፡፡
7የሚያዩኝ ሁሉ ይሣለቁብኛል ራሳቸውንም እየነቀነቁ ያፌዙብኛል፡፡
8«በያህዌ ተማምኖአል፤ ያህዌ ያድነው፤ በእርሱ ደስ ተሰኝቶበታልና እስቲ ይታደገው» ይላሉ፡፡
9አንተ ከእናቴ ማሕፀን አወጣኸኝ በእናቴም ጡት ሳለሁ በአንተ እንድታመን አደረግኸኝ፡፡
10ከማሕፀን ጀምሮ በአንተ ተጣልሁ በእናቴ ማሕፀን ከነበርኩበት ጊዜ ጀምሮ አንተ አምላኬ ነህ!
11መከራ እየተቃረበ ነው የሚረዳኝም የለምና ከእኔ አትራቅ፡፡
12ብዙ ኮርማዎች ከበቡኝ ኃይለኛ የባሳን ኮርማዎች ዙሪያዬን ቆመዋል፡፡
13እንደሚያገሣና እንደሚቦጫጭቅ አንበሳ አፋቸውን ከፈቱብኝ፡፡
14እንደ ውሃ ፈሰሰሁ አጥንቶቼም ሁሉ ከመጋጠሚያቸው ወለቁ ልቤ እንደ ሰም ሆነ በውስጤም ቀጠለ፡፡
15ጉልበቴ እንደ ሸክላ ደረቀ ምላሴም ከላንቃዬ ጋር ተጣበቀ፡፡ እንደ ሞተ ሰው ትቢያ ላይ አደረግኸኝ፡፡
16ውሾች ከበቡኝ የክፉዎች ስብስብ በዙሪያዬ ሰፈሩ፤ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩ
17ዐጥንቶቼን ሁሉ አንድ አንድ መቁጠር እችላለሁ እነርሱም አፍጥጠው ይመለከቱኛል፡፡
18ልብሶቼን ተከፋፈሉ በእጄ ጠባቤም ዕጣ ተጣጣሉ፡፡
19ያህዌ ሆይ፣ ከእኔ አትራቅ ብርታቴ ሆይ፣ እባክህ እኔን ለመርዳት ፍጠን!
20ነፍሴን ከሰይፍ ታደጋት ውድ ሕይወቴንም ከክፉ ውሾች አድናት፡፡
21ከአንበሳ አፍ አድነኝ፣ ከተዋጊ ጐሽ ቀንዶችም ታደገኝ፡፡
22ስምህን ለወንድሞቼ እናገራለሁ፤ በጉባኤም መካከል አመሰግንሃለሁ፡፡
23እናንት ያህዌን የምትፈሩ አመስግኑት፡፡ እናንት የያዕቆብ ዘሮች ሁሉ አክብሩት! እናንት የእስራኤል ልጆች ሁሉ እርሱን ፍሩት!
24ጭንቀት የደረሰበትን ሰው አልናቀም፤ መከራ ላይ ያለውን አልተጸየፈም፤ ነገር ግን የድረሱልኝ ጩኸቱን ሰማው፡፡
25ስለ ሠራኸው መልካም ሥራ፣ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ አመሰግንሃለሁ፤ በሚፈሩህ ሰዎችም ፊት ስእለቴን እፈጽማለሁ፡፡
26ችግረኞች ይበላሉ፤ ይጠግባሉም ያህዌን የሚፈልጉም ያመሰግኑታል፡፡ ልባችሁ ለዘላለም ሕያው ይሁን፡፡
27የምድር ሕዝቦች ሁሉ ያስታውሳሉ ወደ ያህዌም ይመለሳሉ፤ የምድር ወገኖች ሁሉ በፊትህ ወድቀው ይሰግዳሉ፡፡
28መንግሥት የያህዌ ነውና ሕዝቦችንም የሚገዛ እርሱ ነው፡፡
29የምድር ከበርቴዎች ሁሉ ይበላሉ፤ እርሱንም ያመልካሉ በሕይወት ማቆየት የማይችሉ ወደ አፈር ተመላሽ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በፊቱ ይንበረከካሉ፡፡
30የሚመጣው ትውልድ ያገለግለዋል ለቀጣዩ ትውልድም ስለ ጌታ ይነግረዋል
31የጽድቅ ሥራውን በማወጅ ገና ላልተወለደ ሕዝብ ጽድቁን፣ እርሱ ያደረገውንም ይነግራሉ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።